የደም ቧንቧ መድረቅ (ጥበት) – ከጋንግሪን እስከ እግር መቆረጥ የሚያደርሰው የጤና ችግር

                                

ባለታሪካችን ችግሩ የገጠማቸው ከስድስት ዓመት በፊት ነበር፡፡ ከቀበቶ መታጠቂያቸው እስከ እግራቸው የጥፍር ጫፍ ድረስ የህመም ስሜት ይሰማቸዋል፡፡ ህመሙ ደግሞ በየጊዜው የሚጨምር እና እየሄደ የሚመጣ ነው፡፡ ከስድስት ዓመት በፊት ለጀመራቸው የእግር ህመም በራሳቸው ማስታገሻ መድሃኒቶችን በመውሰድ፣ በተጨማሪም ፍልውሃ በመግባትና በመታሸት ለህመማቸው መፍትሄ ለማግኘት ከሁለት ዓመት በላይ ጥረት አድርገዋል፡፡ የህመሙ ስቃይ እየባሰ ሲሄድ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ አስፈላጊ የሚባለውን ህክምና ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን ይሄ ነው የሚባል መፍትሄ ማግኘት አልቻሉም፡፡

በሽታው ተባብሶ የእግር አውራ ጣታቸው እየደረቀና እየጠቆረ ሄደ፡፡ ቀስ በቀስም መራመድ እያቃታቸው ይመጣል፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን ሰውየውም ሆኑ በተለያዩ የጤና ተቋማት ህክምና ያደረጉላቸው ሐኪሞች የችግሩን ምንነት ማወቅ አልቻሉም ነበር፡፡ ጥቁረቱ ከአውራ ጣታቸው አልፎ ቁርጭምጭሚታቸው ላይ ሲደርስ በአንድ ሆስፒታል በተደረገላቸው ህክምና የደም ቧንቧ ድርቀት (ጥበት) እንዳጋጠማቸው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ችግሩ ወደ ጋንግሪን ተቀይሮ ነበር፡፡ ጋንግሪኑ ከጉልበታቸው ስላለፈ አንድ እግራቸው እንዲቆረጥ ይደረጋል፡፡ አሳዛኙ ጉዳይ ችግሩ እግራቸውን በማስቆረጥ ብቻ አለማብቃቱ ነው፡፡ ጋንግሪኑን ከአንድ እግራቸው ተሻግሮ ሌላኛውን እግራቸውን ብቻ የሚጠባበቁ አሳዛኝ አባት ሆነዋል፡፡ የደም ቧንቧ ድርቀት፣ በፍጥነት ምልክት የማያሳይና ድምፅ አልባ አስከፊ የጤና ችግር ነው፡፡ በደም ቧንቧ ድርቀት እንደ እኚህ ባለታሪካችን ሁሉ በርካታ ሰዎች ችግሩን ሳይገነዘቡት ለከፋ ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ አንዳንድ ጥናቶች እንዳረጋገጡት፣ ከአደጋና ከኢንፌክሽን ቀጥሎ በሶስተኛ ደረጃ አካል ጉዳተኝነትን የሚያመጣው የደም ቧንቧ ድርቀት (ጥበት) ነው፡፡ በዚህ የጤና ችግር ዙሪያ ሐኪም አነጋግረናል፡፡ በደም ቧንቧ መድረቅ (ጥበት) ምንነት፣ መንስኤ፣ አጋላጭ ምክንያቶች፣ መፍትሄው፣ በመከላከያውና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርገናል፡፡

 

ጥያቄ፡– ስለደም ቧንቧ ምንነት የተወሰኑ ሐሳቦችን ብናነሳ ጠቃሚ ይመስለኛል…?

መልስ፡- ሁለት አይነት የደም ቧንቧዎች አሉ፡፡ ኦክስጅን የተሸከሙና ደምን ከልብ ወደ ሌላው የሰውነት ክፍል የሚወስዱ የደም ቧንቧዎች አርተሪ ይባላሉ፡፡ ጥቅም ላይ የዋለውን ደም ከሌላው የሰውነት ክፍል ወደ ልብ የሚመልሱ ቧንቧዎች ደግሞ ቬን ይባላሉ፡፡ ደም መልሶችም ሆኑ ደም ቅዳ ቧንቧዎች፣ በሁሉም የሰውነታችን ክፍሎች የሚገኙ ናቸው፡፡ የደም ቧንቧ እንደ አንድ ቲዩብ ብናየውና እኩል ብንቆርጠው ግድግዳውን ማየት እንችላለን፡፡ ደም ቅዳ ቧንቧ ግድግዳው ወፍራም ነው፡፡ የውስጠኛው፣ መካከለኛውና የላይኛው ተብለው የሚከፋፈሉ ሶስት ሌየሮች አሉት፡፡

ጥያቄ፡– የደም ቧንቧ (መድረቅጥበት፣ ራሱን የቻለ በሽታ ነው ወይስ የሌሎች በሽታዎች ምልክት ነው?

መልስ፡- የደም ቧንቧ መድረቅ (መጥበብ) ራሱን የቻለ በሽታ ነው፡፡ ኦክስጅን ያለው ደም ከልብ ወደ ሌሎች አካሎች የሚወስዱት አርተሪዎች፣ ግድግዳቸው ለስላሳ የነበረው እየደረቀ ወደ ጠጣርነት ይለወጣሉ፡፡ ድርቀቱ አንዳንድ ጊዜ አጭር ቦታ የሚሸፍን ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከቀበቶ መታጠቂያ እስከ እግር ጣት ጫፍ ድረስ ችግሩ ሊከሰት ይችላል፡፡

ጥያቄ፡– መንስኤው ምንድነው?

መልስ፡- የደም ቧንቧ (መድረቅ) ጥበት ይሄ ነው ተብሎ የሚታወቅ መንስኤ ባይኖረውም አንዳንድ መላምቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ የውስጠኛው የደም ቧንቧ ግድግዳ በተለያዩ ምክንያቶች ሊቆስል ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ለመዳን በሚያደርገው ጥረት የደም መርጋትና ካልሽየም እንዲጠራቀም የማድረግ ሁኔታን ያመጣል፡፡ እንደዚሁም በተለያዩ ምክንያቶች የሚደርስ አደጋ ለደም ቧንቧ መድረቅ (መጥበብ) መንስኤ ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በመላምት ደረጃ ያሉ እንጂ የተረጋገጡ መንስኤዎች ናቸው ማለት አይቻልም፡፡

ጥያቄ፡– አጋላጭ ምክንያቶችስ?

መልስ፡- በግልፅ የሚታወቁ አጋላጭ ምክንያቶች አሉ፡፡ የደም ቧንቧ ግድግዳ ለስላሳ (ኢላስቲክ) መሆን ሲገባው ጥንክር (ድርቅ) የማለት ሁኔታ ያሳያል፡፡ በደም ቧንቧው ውስጥ ካልሽየም በብዛት በመጠራቀሙ ምክንያት፣ ግድግዳው ከቀላል መድረቅ ጀምሮ እንደ ብረት ጠንካራ እስከ መሆን ሊያደርሰው ይችላል፡፡ በአጠቃላይ ለደም ቧንቧ በሽታ አጋላጭ ከሚባሉ ምክንያቶች መካከል ዋነኛ የሚባሉት የሚከተሉት ናቸው፡፡

– ዕድሜ መጨመር፤

– በደም ውስጥ የካልሽየም ንጥረ ነገር መከማቸት፤

– የኩላሊት ከስራ ውጭ መሆን (የኩላሊት ፌለሪቲ ያጋጠማቸው)፤

– የደም ብዛት ያለባቸው፤

– በተለያዩ ምክንያቶች የደም ቧንቧ ላይ ጉዳት ሲደርስ፤

– በደም ውስጥ የኮሌስትሮን መጠን ከፍተኛ ደረጃ መድረስና

– ሲጋራ ማጨስ፣ ለደም ቧንቧ መድረቅ በቀዳሚነት የሚያጋልጡ ምክንያቶች ናቸው፡፡

ጥያቄ፡– ስርጭቱ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

መልስ፡- ከድንገተኛ አደጋ ቀጥሎ እግሮቻችንን ከሚያሳጡን ችግሮች ውስጥ የደም ቧንቧ ጥበት ወይም ድርቀት አንዱ ነው፡፡ ችግሩ በአገራችንም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የህብረተሰብ ክፍል የሚያጠቃ ነው፡፡ በተለይም ረጅም ዕድሜ የሚኖሩ ሰዎች በሚበዙባቸው አገሮች በሽታው በስፋት ይታያል፡፡ በአሜሪካ ያለውን መረጃ እንኳ ስናይ በየዓመቱ ከ350,000 በላይ ሰዎች በደም ቧንቧ ጥበት (ድርቀት) ይታመማሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከ25,000 በላይ ሰዎች እግራቸውን ያጣሉ፡፡ በሀገራችን ቁጥሩ ምን ያህል እንደሆነ የሚያሳይ መረጃ የለም፡፡ ወደ ጤና ተቋማት የሚመጡትን ህሙማን ስናይ ግን ቁጥሩ በየጊዜው በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመሄድ ላይ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በአገራችን ከአደጋና ከኢንፌክሽን ቀጥሎ አካልን በተለይም እግርን ለማጣት መንስኤ የሚሆነው የደም ቧንቧ መድረቅ (ጥበት) ነው፡፡

ጥያቄ፡– በተለየ ሁኔታ የሚያጠቃው የህብረተሰብ ክፍል አለ?

መልስ፡- የደም ቧንቧ መድረቅ (መጥበብ) በሁሉም ሰው ላይ የሚታይ ሳይሆን በአብዛኛው ከ40 እስከ 50፣ ከ50 እስከ 69 በሚገኙ የዕድሜ እርከኖች ከአስር እስከ አስራ አምስት በመቶ የመጋለጥ ዕድል ሲኖር ከ70 ዓመት በኋላ ከ25 በመቶ በላይ የመጋለጥ ዕድል ይኖራል፡፡ ከሴቶች ይልቅ ወንዶች ለደም ቧንቧ መድረቅ (መጥበብ) የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡  ከነጮች ይልቅ ጥቁሮች (አፍሪካውያን) በተለየ ሁኔታ ይጠቃሉ፡፡

ጥያቄ፡– በሽታው ደረጃዎች ካሉት ቢገልፁልኝ?

መልስ፡- ህመሙ አራት ደረጃዎች አሉት፡፡ በሽታው እያለ ምንም አይነት ምልክት የማያሳይ ከሆነ ደረጃ አንድ እንለዋለን፡፡ በእንቅስቃሴ ወቅት የህመም ስሜት የሚታይ ከሆነ ደረጃ ሁለት፣ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ሳይኖር ህመም ካለ ደረጃ ሶስት ሲባል፣ ቁስለት ካመጣ ደረጃ አራት ወይም አስጊ ደረጃ የደረሰ እንለዋለን፡፡

ጥያቄ፡– በሽታው ሲከሰት የሚታዩ ምልክቶች የትኞቹ ናቸው?

መልስ፡- በሽታው ሲከሰት አንዳንድ ጊዜ ምንም ምልክት ላያሳይ ይችላል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በየደረጃው የሚታዩ ምልክቶች አሉ፡፡ ዋና ዋና የሚባሉትን እንያቸው፡፡

– በእንቅስቃሴ ወቅት የደም ቧንቧ ከተዘጋበት ቦታ ጀምሮ ባትና መቀመጫ አካባቢ ህመም ይኖራል፤

– የእግር ህመም፤

– የቆዳ ቀለም መጥቆር፤

– ከታፋ ጀምሮ እስከ መጫሚያ ድረስ ህመም ይኖራል፤

– የደም ስር ትርታ መዳከም፤

– የደም ዝውውር መቀነስ፤

– የተለያዩ ቁስሎች ሲፈጠሩ አለመዳን፤

– የቆዳ መቀዝቀዝ፤

– የቆዳ መብለጭለጭ፤

– እጅና እግር አካባቢ ያሉ ፀጉሮች መብነን፤

– የጥፍር ቀለም መለወጥና ቶሎ ቶሎ መሰባበር፤

– እግር ወደ ላይ ሲሰቀል ወይም ደግሞ ሲዘቀዘቅ ህመም ሊከሰት ይችላል፡፡

ጥያቄ፡– የደም ቧንቧ መድረቅ (መጥበብመከሰቱን ለማረጋገጥ የሚሰሩ ምርመራዎችስ?

መልስ፡- በሽታው መኖር አለመኖሩን የማረጋገጥ ጉዳይ ከባድ አይደለም፡፡ የምርመራው መጀመሪያ ህመምተኛው ስለበሽታው ከሚነግረንና አጋላጭ ምክንያቶች መኖራቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ አካላዊ ምርመራ በማድረግ የደም ቧንቧ መድረቅ (ጥበት) በሽታ መከሰቱን ከ75 እስከ 80 በመቶ ድረስ እንገምታለን፡፡ እንደዚሁም የደም ቧንቧን የመለካት ምርመራ በማድረግ ግምታችንን 90 በመቶ ማድረስ ይቻላል፡፡ በትክክል በሽታ ተከስቷል ብሎ እርግጠኛ ለመሆን የሚያስችለን የዶፕለር አልትራ ሳውንድ ምርመራ ነው፡፡ በዚህ የምርመራ ዘዴ የደም ቧንቧዎችን ከመነሻቸው እስከ መድረሻቸው ድረስ ያለውን ሁኔታ የማየት ችሎታ አለው፡፡ የደም ቧንቧው ንዝረትን፣ በውስጡ የሚያልፈውን የደም ብዛትና የደም ቧንቧው ግድግዳ ምን ያህል እንደጠበበ መለካት ያስችላል፡፡

ጥያቄ፡– በህክምና ያለው መፍትሄ ምንድነው?

መልስ፡- በሀገራችን ገብተው ጥቅም ላይ ባይውሉም በውጭው ዓለም የጠበበውን የደም ቧንቧ የሚያሰፉ መድሃኒቶች አሉ፡፡ በጣም ጥሩ የሚባል ለውጥ የማምጣት አቅም ያላቸው ናቸው፡፡ ሁለተኛው ምንም አይነት ቀዶ ህክምና ሳይደረግ በቆዳ በኩል አነስተኛ ቀዳዳ በመክፈትና ቲዩብ በማስገባት፣ የጠበበውን የደም ቧንቧ የማስፋት ወይም የመሰንጠቅ ህክምና ይሰጣል፡፡ ሶስተኛው የህክምና ዓይነት በቀዶ ህክምና የጠበበውን የደም ቧንቧ በመቀየር ‹ባይባስ› በመስራት ማከም ይቻላል፡፡ ይሄን ህክምና ግልጽ ለማድረግ ለምሳሌ አንድ መንገድ የሆነ ቦታ ቢሰበር ሌላ አቋራጭ መንገድ እንደምንፈልግለት ሁሉ፣ ሌሎች የደም ቧንቧዎችን በመቀጣጠል ደም በሌላ አቅጣጫ የተፈለገው ቦታ እንዲደርስ የምናደርግበት የህክም ዘዴ ዘዴ ‹ባይፓስ› ይባላል፡፡ ከእነዚህ ህክምናዎች ውስጥ በሀገራችን የሚሰጠው በቀዶ ህክምና ባይፓስ መስራት ነው፡፡ ሁለቱ ህክምናዎች በአገራችን አይሰጡም፡፡ ህክምናው ቀለል ያለ ቢሆንም ህመምተኞቹ የሚመጡት በሽታው ጋንግሪን ከፈጠረ በኋላ ነው፡፡ በሽታው እዚህ ላይ ሲደርስ ህክምናውን መስጠት ከባድ ከመሆኑም በላይ የሚገኘው ውጤትም በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡

ጥያቄ፡– የደም ቧንቧ መድረቅ (መጥበብበወቅቱ ካልታከመ የሚያስከትለው ጉዳት ምንድነው?

መልስ፡- የማያቋርጥ ስቃይ ያመጣል፣  መራመድን ይከለክላል፤ በስተመጨረሻም ከአውራጣት ጀምሮ አጠቃላይ እግርን እስከ ማሳጣት የሚደርስ ጉዳትን ያመጣል፡፡

ጥያቄ፡– ብዙ ሰው ጋንግሪንን ከስኳር በሽታ ጋር ብቻ ነው የሚያይይዘው ከተሳሳትኩኝ…?

መልስ፡- ልክ ነህ፤ የአስተሳሰብ ችግር ስላለ ነው እንጂ ከስኳር በሽታ በላይ የደም ቧንቧ መድረቅ (ጥበት) ነው ጋንግሪን የሚያመጣው፡፡ እንደ ስኳር በሽታ ብዙ አይታወቅም፡፡ ቀስ በቀስ የሚመጣ ከመሆኑም በላይ ከላይ የሚታይ አይደለም፡፡ ነገር ግን እግርን በማሳጣት ከስኳር በሽታም የበለጠ ነው፡፡

ጥያቄ፡– ጋንግሪን ከደም ቧንቧ መድረቅ (ጥበት) ከስኳር በሽታ ጋር ያለው ግንኙነት ምንድነውስኳርና የደም ቧንቧአንድ ላይየመከሰት ዕድል አላቸው?

መልስ፡- ጋንግሪን በስኳር በሽታ፣ በደም ቧንቧ ጥበት፣ በአደጋ፣ በኢንፌክሽንና በካንሰር ምክንያት ኦክስጅን ያለው ደም የማይደርሰው አካል መሞት ማለት ነው፡፡ የስኳር በሽታና የደም ቧንቧ ጥበት (መድረቅ) በአንድ ሰው ላይ በአንድ ጊዜ የመከሰት ዕድል አላቸው፡፡ የደም ቧንቧ መድረቅ ጋንግሪንን የሚያመጣበት ምክንያት የቧንቧ ጥበት ስላለና ደም በአግባቡ ስለማይደርስ ነው፡፡ ስኳር ጋንግሪንን የሚያመጣው የደም ቧንቧ ጥበት ስላለ ሳይሆን የሰውነት መከላከያ አቅም ያጣል፡፡ በዚህም ምክንያት ቁስል ይፈጠራል፡፡ የተፈጠረው ቁስል ነው ወደ ጋንግሪን የሚለወጠው፡፡ ጋንግሪን ብዙውን ጊዜ እግር ላይ የሚከሰት ቢሆንም፣ አልፎ አልፎ እጅ ላይ የሚታይ መሆኑን መገንዘብ ጠቃሚ ይሆናል፡፡

ጥያቄ፡– እንዴት እንከላከል?

መልስ፡- ባት፣ መቀመጫ እና ጣት አካባቢ የህመም ስሜት ካለ በፍጥነት ወደ ህክምና መሄድ ያስፈልጋል፡፡ ሌላው በሽታው ቀላል ባለመሆኑ ስለበሽታው በቂ ግንዛቤ በህብረተሰቡ ውስጥ እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሲጋራ አለማጨስ፣ ደም ግፊትን በአግባቡ መቆጣጠር፣ ኮሌስትሮልን እና ሌሎች በሰውነት ውስጥ ያሉ የቅባት መጠኖች ከፍ እንዳይሉ ማድረግና አካላዊ እንቅስቃሴ አዘውትሮ በማድረግ የደም ቧንቧ መድረቅን (መጥበብን) መከላከል ይቻላል፡፡

ምንጭ፦Mahdere Tena

Advertisement