እናቶች ለምን ልጆቻቸውን በግራ ጎን ማዘል ያዘወትራሉ?

                                       

ልጅዎን በግራ ጎን በኩል ማዘል ይቀናዎታል?፤ ልጅን በግራ ጎን በኩል ማዘል በብዛት የሚዘወተር ሲሆን፥ ምክንያቱን ግን አስበን አናውቅም።

ተመራማሪዎች ግን እናቶች ለምን ልጃቸውን በግራ ጎናቸው በኩል መሸከም ያዘወትራሉ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ አግኝተናል እያሉ ነው።

ምንም እንኳ ልጅን በቀኝ በኩልም ይሁን በግራ በኩል ማዘል የሚያስከትለው ችግር ባይኖርም፤ አብዛኛዎቹ እናቶች ግን ልጃቸውን በግራ ጎናቸው ማዘል ይቀናቸዋል ይላሉ ተመራማሪዎቹ።

ከዚህ ቀደም በተሰሩ ጥናቶችም 85 በመቶ የሚሆኑት እናቶች ልጃቸውን በግራ ጎናቸው በኩል ማዘልን እንደሚያዘወትሩ አመልክቷል።

ሆኖም ግን ከዚህ ልማድ ጀርባ ያለው ምክንያት እስካሁን አይታወቅም ነበር።

የዚህም ምክንያት ለማግኘትም የሩሲያ ቅዱስ ፒተርስበርግ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች እንዲህ አይነት ልማድ እንስሳቶች ላይ እንደሚስተዋል የተመከቱ ሲሆን፥ በዚህም ልጅን በግራ ማዘል ልማድን ሰዎች ያመጡት ነው አሊያም በሁሉም ፍጥረታት ዘንድ የሚስተዋል ነው የሚለውን ተመልክተዋል።

በዚህም ዋልሩስስ የተባለው የባህር እንስሳ እና የሌሊት ወፍ ልክ እንደ ሰው ሁሉ ልጃቸውን በግራ ጎን አዘውትረው ማዘል እንደሚቀናቸው መለየታቸውን ነው ተመራማሪዎቹ ያስታወቁት።

ተመራማሪዎቹ ጥናቱ ላይ ተመስርተው ባስቀመጡት ድምዳሜም ልጅን በግራ በኩል የማዘል ልማድ በዝግመተ ለውጥ የመጣ እና በልጆች እና በወላጆች መካከል ስሜታዊ የሆነ ግንኙነት እንዲፈጠር ሊረዳ ይችላል ብለዋል።

ልጅን በግራ በኩል ማዘል በምን መልኩ ከልጆቻችን ጋር ስሜታዊ የሆነ ግንኙነት እንዲፈጠር ያደርጋል የሚለውን ለመረዳት ደግሞ አእምሯችንን መመልከት መልካም ነው ይላሉ።

የቀኝ አእምሯችን ክፍል በግራ በኩል ያለው የሰውነታችን ክፍል ስራውን በአግባቡ እንዲሰራ የሚያስተባብር ሲሆን፥ በተጨማሪም ሂደቶችን እና ስሜቶችን በቀላሉ እንድንረዳ የሚያደርግ የአእምሮ ክፍል ነው።

እንደ ተመራማሪዎቹ ገለጻ፥ እናቶች ልጃቸውን በግራ ጎናቸው በሚያዝሉበት ጊዜ ከግራ የአእምሯቸው ክፍል ጋር ያለው ግንኙነት እንዲጨምር ያደርጋል።

በዚህ ጊዜም እናቶች ለልጆቻቸው የሚያስፈልገውን ነገር በፍጥነት ተረድተው እንዲያስተካክሉ ያደርጋል ይላሉ ተመራማሪዎቹ በሰጡት ማብራሪያ።

Advertisement