ፍቅር እና ግንኙነት ከቲንደር አብዮት በኋላ – Love and Relationship After The Tingeing Revolution

                          

ምን ያህል ጥንዶች በበይነ-መረብ በዘንድሮው የፍቅረኞች ቀን ተገናኙ? ‘ከዚህ ቀደሙ የሚበልጥ’ የሚለው ምላሽ ችግር የሌለው መልስ ነው። ምክንያቱም በበይነ-መረብ ፍቅረኛን የማፈላለግ ሥራ በመላው ዓለም በመጠናከሩ ነው።

ግን በይነ-መረብ የፍቅር ጓደኛን ለማግኘት ምርጡ መንገድ ነው?

በቀጣይ የኮምፒውተር መረጃ ከማን ጋር በፍቅረኛነት አብረው እንደሆኑ እና ምን ያህል ጊዜ አብረው እንደቆዩ ማወቅ ይቻላል። ይህ እንደሚሆን ከወራት በፊት ብላክ ሚረር በተሰኘው የቴሌቪዥን ተከታታይ ፕሮግራም ተገልጿል።

ከወዲሁ ግን ቴክኖሎጂ ፍቅርን ቀይሮታል። በ1990ዎቹ አጋማሽ ማች ዶት ኮም ከጀመረው በኋላ በበይነ-መረብ ፍቅረኛን መፈለግ በከፍተኛ ደረጃ ተስፋፍቷል።

እንደቲንደር ያሉ መተግበሪያዎች ደግሞ እንደአዲስ ለመቀላቀል ቀላል በመሆናቸው እና ፍቅረኛ የመፈለግን አካሄድ በማቅለላቸው ወደሌላ ደረጃ አድርሰውታል።

ቲንደር የስማርት ስልኮች መምጣትን ተከትሎ በአውሮፓዊያኑ 2012 ነበር የተጀመረው። ከሁለት ዓመት በኋላ በቀን ሁለት ቢሊዮን ጎብኚዎችን ማግኘት ችሏል።

ባለፈው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዴሞክራቶች ለምርጫ ቅስቀሳም ይህንኑ ተጠቅመውበታል።

የ24 ዓመቷ ጦማሪ ጆርዳን ብራውን እንደምትለው በአውሮፓዊያኑ 2016 በይነ-መረብን በመጠቀም ነበር ከምትኖርበት አካባቢ ብዙም የማይርቀውን ፍቅረኛዋን ያገኘችው። ይህ ባይሆን ኖሮ ላይገናኙ እንደሚችሉ ጠቅሳ ሁለቱም ዲዝኒን መውደዳቸው ደግሞ ይበልጥ እንዳቀራረባቸው አስታውቃለች።

የ30 ዓመቷ ሳራ ስካረሌት በአውሮፓዊያኑ 2015 ወደ ዱባይ ስታቀና ከአዳዲስ ሰዎች ጋር ለመገናኘት ነው የቲንደር አባል የሆነችው። የቀድሞ የወንድ ፍቅረኛዋንም ከአንድ ወር በኋላ ነበር ያገኘችው። ከምታወራቸው ሰዎች ጋር መገናኘት ግን አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሳለች።

“ለረዥም ጊዜ ከእነሱ ጋር የጽሑፍ መልዕክት ብትለዋወጥም ተገናኝቶ ቡና ለመጠጣት እንኳን ፍላጎት የላቸውም” ትላለች።


ሌሎችም አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንዳሉ ጆርዳን ትናገራለች።

“በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዓታቸውን ለማጥፋት የሚፈልጉ እና ሥራ ፈቶች ስላሉ ኑሮህን ከማዘበራረቅ ውጭ ምንም አይሰሩም” ብላ የታዘበችውን ትገልጻለች።

ከእነዚህ ሁሉ ችግሮች ጋርም ቢሆን ፍቅረኛን ማፈላለጊያ በይነ-መረቦች በከፍተኛ ደረጃ እያደጉ ነው። አፕ አኒ እንደተባለ ተቋም ጥናት ከሆነ በአውሮፓዊያኑ 2016 በእነዚህ በይነ-መረቦች 234 ቢሊዮን ፓውንድ ወጪ የተደረገ ሲሆን ይህ አሃዝ በ2017 ወደ 448 ከፍ ብሏል።

59 በመቶ የሚሆኑ አዋቂዎች ፍቅረኛን ማፈላለጊያ በበይነ-መረቦች አዳዲስ ሰዎችን ለማግኘት ጥሩ ናቸው ብለው እንደሚያምኑ የፒው ጥናት ይጠቁማል።

በበይነ-መረብ ጥንዶችን ማፈላለጊያ መንገዶች በተለይም የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ በሞት በሚያስቀጣባቸው ሃገራት ላሉ የተመሳሳይ ጾታ ጥንድ ፈላጊዎች ጠቃሚ መሆኑን ግራይነደሩ ጃክ ሃሪሰን-ኩይታና አስታውቀዋል።

በአፕ አኒ ውስጥ ዳይሬክተር በመሆን በማገልገል ላይ የሚገኙት ፖል ባርነስ እንደሚሉት እንግሊዝ ውስጥ ባለፈው ዓመት ተገልጋዮች በብዛት ከተጠቀሟቸው 10 መተግበሪያዎች ውስጥ ሶስቱ የፍቅረኛ ማፈላለጊያ መተግበሪያዎች ናቸው።

“እዚህ በጣም ብዙ ገንዘብ ስላለ አሁን በጣም ብዙ ፉክክርም አለ” ይላሉ ባርነስ። “ስለዚህ መተግበሪያ ሰሪዎች ተጠቃሚዎቻቸውን በደንብ ማወቅ እና በይበልጥ የሚሳተፉበትን መንገድ ሊፈጥሩ ይገባል” ብለዋል።

ቀደም ሲል የፍቅረኛ የማፈላለግ አገልግሎት ሰጪዎች አባል መሆን የሚፈልጉ በጣም ብዙ ጥያቄዎችን እንዲመልሱ ይጠብቁባቸው ነበር። አሁን ግን ማሽኖች የበለጠ ሊስማሙ የሚችሉ ተፈላላጊዎችን በማገናኘቱ በኩል ይሰራሉ።

ትዊተር ላይ አንድ ሰው የሚጽፈውን ከ300 እስከ 400 የሚደርስ ቃል ያለውን ነገር በማገናዘብ ማሽኑ ምን ያህል ሁለት ሰዎች የጋራ ነገር እንዳላቸው ለማወቅ ይችላል ይላሉ የላቭፍላተር ተባባረሪ መስራች ዲያጎ ስሚዝ።

ላቭፍላተር መቀመጫውን ቶሮንቶ ካደረገ እና ሪሲፕቲቪቲ ከተሰኘ የቋንቋ ጥናት ተቋም ጋር በመቀናጀት የሚመሳሰሉ ሰዎችን ለመለየት የሚያሰችላቸውን አዲስ ዘዴ ፈጠሩ ሲሆን በዘንድሮው ዓመትም ተግባራዊ ይደረጋል።

ይህም በኦስቲን ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ስነልቦና ፕሮፌሰር የሆኑት ጀምስ ፔንቤከር ጥናት እንዲያደርጉ አነሳስቷቸዋል። ፕሮፌሰር ፔንቤከር በ86 ጥንዶች ላይ ባደረጉት ጥናት ተመሳሳይ ቃላትን፣ ሀረጎችና እና ሌሎች የቋንቋ አጠቃቀሞችን የሚጋሩት ከሶስት ወራት በላይ አብረው የመቆታቸው ዕድል ከፍተኛ ነው።


ሌላኛው ዘዴ ደግሞ ስማርት ስልኮችን ቦታ ጠቋሚ በመጠቀም ጥንዶችን የማገናኘት ስራ ነው።

መቀመጫውን ፓሪስ ያደረገው ሃፕን የተሰኘ የመተግበሪያ ተቋም ቀኑን ያሳለፉበትን አካባቢ ያጣናል። ከዚም ከእርሶ በ250 ሜትር ርቀት ውስጥ ያለፉ ሰዎችን ማንነት ያሳይዎታል። እነዚህን ሰዎች በእውኑ ዓለም ማግኘት በጣም ቀላል መሆኑን የተቋሙ ባልደረባ የሆኑት ክሌይር ሰርቴይን ይገልጻሉ።

“ዋናው ነገር መገናኘት እና መሞከር ነው። የተገናኙት ሰዎች መጣጣም ወይም አለመጣጣማቸው ምስጢራዊ እና በጣም አስገራሚ ነገር ነው።”

ሆኖም በቅርብ ርቀት መኖር የትዳር አጋርን መፈለግን ችግር ሚፈታው ከሆነ ባለን ማህበራዊ አካባቢ ብቻ እንድንታጠር ያደርገናል ሲሉ የሶሶሊጂ ባለሙያው ጁስዉ ኦርቴጋ ያስጠነቅቃሉ። በበይነ-መረብ ፍቅረኛን ማፈላለግ ከተለያየ ዘር የመጡ ሰዎችን እያገናኘ መሆኑን ጠቁመዋል።

በካምብሪጅ ዩኒቨርሰቲ የማስተርስ ተማሪ እያለች ስለቲንደር ያጠናችው ራቼል ካትዝ አሁን ደግሞ ለዶክተሬት ዲግሪዋ በግራይነደር ዙሪያ እያጠናች ሲሆን በሃሳቡ ትስማማለች።

“በአንድ ወቅት ሰዎች በአቅራቢያቸው ከሚገኙ ሰዎች ጋር ብቻ ነበር የሚጋቡት። በይነ-መረብ ከመስፋፋቱ ጋር ተያይዞ ይህ ነገር ከየትኛውም ዓለም ክፍል ካሉ ሰዎች ጋር ሊሆን ችሏል።”

በ2018 ደግሞ የመኖሪያ አካባቢ አሁንም በድጋሚ ወሳኝ ጉዳይ ሆኗል ይላሉ ካትዝ። “ስለዚህ በጣም ከሚቀርብዎት ሰው ጋር ይገናኛሉ ማለት ነው። ይህ ደግሞ የደረጃ ልዩነትንም ያካትታል።”

እንደባለሙያዎች ከሆነ የትዳር አጋርን የሚያገናኙ በይነ-መረቦች ከፍተኛ የቴክኖሎጂ አሠራሮችን ያካተቱ ይሆናሉ ይላሉ።

አስቡት እስኪ በመዝናኛ ስፍራ ያሉትን ሰዎች በስልክዎ ስካን በማድረግ በይነ-መረብ ፍቅረኛ ለመፈለግ መመዝገብ አለመመዝገባቸውን ማወቅ ይችላሉ ሲሉ ክሌር ሰርቴይን ይገልጻሉ።

በእነዚህ የበይነ-መረብ ፍቅረኛ ማፈላለጊያ መተግበሪያዎች ላይ ከሚነሱት ችግሮች መካከል ለሴቶች ምቹ አይደሉም መባሉ ነው።

የዋንስ ዴቲንግ መስራች እና ዋና ስራ አስፈጻሚ ጂን ሜየር እንደሚሉት በፍቅረኛ ማፈላለጊያ በይነ-መረቦች ላይ የሚገኙ ሴቶች ቁጥር ከ35 በመቶ በጭራሽ በልጦ አያውቅም ይላሉ። ወንዶችም አንዳንድ ጊዜ እንደወንዶች ራሳቸውን አያቀርቡም።

በእነሜየር መተግበሪያ ላይ ሴቶች ስለሚገጥሟቸው ሴቶች ግብረ-መልስ ይሰጣሉ። ወንዶች ከእነዚህ ምላሾች ሊማሩ ይችላሉ ሲሉ ይገልጻሉ።

ቀድሞ የቲንደር ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት ዎልፍ ሄርድ የመጀመሪያ ግንኙነታቸውን ከወንድ ጋር ባደረጉ ሴቶች ዙሪያ የሚሰራ በምብል የሚል መተግበሪያ ይፋ አድርገዋል። ከ85 በመቶ በላይ የሚሆኑት የድርጅቱ ሠራተኞች ሴቶች ሲሆኑ እንደፎርብስ ምጽሔት ከሆነ የድርጅቱ ዋጋ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ተገምቷል።

ስለዚህ በበይነ-መረብ ፍቅረኛን ከመፈለግ ቀጠሎ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ተጨምረውበት ቢያስደምሙንም ወደ ፍቅር ስንመጣ ግን ምንም ዋስትና አይሰጡም።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement