ሬክስ ቲለርሰን ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት አጣጣሉ – Rex Tillerson Slams China’s Relationship With Africa

                                                           

የዩናይትድ ስቴትስ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲለርስን ወደ አፍሪካ ሃገራት ከሚያደርጉት ጉዞአቸው በፊት ቻይና ከአፍሪካ ሃገራት ጋር ያላትን የኢኮኖሚያዊ ትብብር ተችተዋል።

በንግግራቸውም ቻይና ጥገኝነትን የምታበረታታ፤ ሕጋዊ ያልሆኑ ስምምነቶችንና የተፈጥሮ ሃብቶችን እየተጠቀመች ነው ብለዋል።

አቶ ሬክስ ቲለርሰን ለአፍሪካ የተመደበውን የ533 ሚሊዮን ዶላር የሰብዓዊ እርዳታ ዕቅድም አሳውቀዋል።

በጉዟቸው ከአፍሪካ ጋር ያለውን ትስስር ለማጠናከር ጥረት ከማድረጋቸውም በተጨማሪ በተለይ ፕሬዚዳንት ትራምፕ አህጉሪቷን ለመግለጽ የተጠቀሙበትን አጸያፊ ቃል ለማስተባበል ይጥራሉ ተብሎ ይታሰባል።

ሬክስ ቲለርሰን ወደ ቻድ፣ ጂቡቲ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ናይጄሪያ ከማምራታቸው በፊት ቨርጂኒያ በሚገኘው የጆርጅ ማሰን ዩኒቨርሲቲ ንግግር አድርገዋል።

ፀረ-ሽብር፣ ዲሞክራሲ፣ አስተዳደር፣ ንግድና ኢንቨስትመንት የጉዟቸው ዋና ዋና ርዕሶች መሆናቸውንም አሳውቀዋል።

ከዚያም ቻይናን ወደ መተቸት ተዛወሩ።

ቻይና የሚታካሄዳቸው ኢንቨስትመንቶች የአህጉሪቱን መሠረተ ልማት ለማሻሻል አቅም እንዳለው የተናሩት ሬክስ፤ የቻይና አቀራረብ ግን ከባድ ዕዳ ያስከተለ መሆኑንና ብዙም የሥራ ዕድል እንዳልፈጠረ ጨምረው ተናግረዋል።

አህጉሪቷ ያሏትን ማዕድናት በመጠቀም ፍላጎት የተገፋፋችው ቻይና፤ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ከአፍሪካ ጋር ያላትን የንግድ ትስስር አፋጥናለች።

ሆኖም ግን የቻይና የመንገድ ግንባታ ተቋማት በተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት ለረዥም ጊዜያት ተዘንግተው በነበሩ መሠረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ማሻሻያዎችን አድርገዋል።

ሬክስ ቲለርሰን ”የሃገራችን ደህንነትና ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና ከድሮ በተለየ መልኩ ከአፍሪካ ጋር የተያያዘ ነው” ብለዋል።

የታሰበውም የእርዳታ ዕቅድ በምግብ እጥረትና በግጭት ለተጠቁ የሶማሊያ፣ የደቡብ ሱዳን፣ የኢትዮጵያና የቻድ ሐይቅ ዳርቻ ሕዝቦች የሚረዳ እንደሆነም ገልጸዋል።

አቶ ሬክስ ቲለርሰን ከዚህ ቀደም የነዳጅ ድርጅት የበላይ ኃላፊ ሆነው በሚሠሩበት ወቅት ወደ አፍሪካ ብዙ ተጉዘው እንደሚያውቁ ተናግረዋል።

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአፍሪካ የሚያደርጉት ጉብኝት የሩሲያው አቻቸው ሰርጌይ ላቭሮቭ በኢትዮጵያ፣ በአንጎላ፣ በሞዛምቢክ፣ በናሚቢያ እና በዚምባብዌ በዚሁ ሳምንት ከሚያደርጉት ጉብኝት ጋር ተገጣጥሟል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement