የሳይንስ መረጃዎቻችን፣ Science Information

                                      

ሕንድ ዶክተሮች የዓለማችን ትልቁ ሳይሆን አይቀርም ያሉትን እጅግ ግዙፍ የአንጎል እጢ በቀዶ ሕክምና ማውጣት መቻላቸው ተዘግቧል፡፡

የ31 ዓመቱ ሕንዳዊ በቀዶ ሕክምና የወጣለት እጢ ክብደት 1.8 ኪሎግራም የሚመዝን ነው ተብሏል፡፡

የቀዶ ሕክምናው 7 ሰዓታት መፍጀቱም ተነግሯል፡፡
የቀዶ ሕክምናውን ያካሄደው የሐኪሞች ቡድን መሪ የሆኑት ዶ/ር ትሪሙርቲ ናድካርኒ፣ “በሽተኛው አሁን ከአደጋ ነፃ ሆኖ በማገገም ላይ ነው” ብለዋል፡፡

ዶ/ሩ አክለውም፣ ቀዶ ሕክምናው በጣም ጥንቃቄ የሚጠይቅ እንደነበር፣ በቀዶ ሕክምናው ወቅትም 11 ዩኒት ደም መጠቀማቸውንና ከቀዶ ሕክምናው በኋላም በሽተኛው ለቀናት ቬልትሌተር አጠገብ እንዲሆን መደረጉን ተናግረዋል፡፡

የቀዶ ሕክምናው የዛሬ 14 ቀን ግድም መካሄዱን የዘገበው ቢቢሲ እስካሁን ስለቀዶ ሕክምናው ያልተነገረው ዶክተሮቹ በቀዶ ሕክምናው መሳካት ላይ እርግጠኛ ስላልነበሩ መሆኑን ገልጿል፡፡

በሽተኛው ከዚህ እጅግ ትልቅ ከሆነ እጢ ጋር ላለፉት 3 ዓመታት ኖሯል፡፡

በእጢው ሳቢያ ሕንዳዊው በሽተኛ የማየት ብቃቱን ማጣቱን የሚገልፁት ዶክተሮቹ አሁን ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ግን የማየት ብቃቱ ይመለስለታል ብለው ተስፋ አድርገዋል::
እጢው የወጣለት ሕንዳዊ ባለቤት ሦስት ሆስፒታሎች ቀዶ ሕክምናውን ለማድረግ አይቻልም ብለዋቸው እንደነበር ተናግራለች፡፡

ሌላው ሰሞኑን ይፋ የሆነ የጥናት ውጤት በድምፅ አካባቢያቸውን መለየት ስለሚችሉ አይነ ሥውራን ይነግረናል፡፡

የሌሊት ወፍ በጨለማ ውስጥ ለማየት ድምፅን እንደምትጠቀም ይታወቃል፡፡ የለሊት ወፍ በጨለማ ውስጥ ድምፅን በመልቀቅ የተለቀቀው ድምፅ ከነገሮች ጋር ተጋጭቶ ሲመጣ የሚሰጠውን የድምፁን የገደል ማሚቶ በማየት፣ ከፊትም ሆነ ከኋላዋ ያለውን ነገር በመለየት መብረር ትችላለች፡፡

Royal Society journal Proceedings B በተባለው የምርምር መፅሄት ላይ የታተመው የጥናት ውጤት፣ ልክ እንደለሊት ወፍ በድምፅ አካባቢያቸውን መለየት እና ማየት ስለሚችሉ ዓይነሥውራን ደረስኩበት ያለውን ይፋ አድርጓል፡፡

ጥናቱ፣ በዚህ “echolocation” በሚሰኘው በድምፅ አካበቢን የማየት ስልት የተራቀቁ ዓይነሥውራን ጠንከር ያለ ድምፅ በማውጣት እንዴት ከኋላቸው ያለን ነገር ምንነት ማወቅ እንደሚችሉ ይፋ አድርጓል፡፡

ሌሎች ጥናቶች እንዳሳዩትም በአፋቸው በሚያወጡት ድምፅ አማካኝነት አንዳንድ በስልቱ የተራቀቁ ዓይነሥውራን በአካባቢያቸው ያሉትን ቁሳቁዎች ቅርፅ፣ መጠን፣ ርቀት እና ዕቃው የተሰራበትን ነገር ጭምር ማወቅ እንደሚችሉ ታውቋል…

በቤተ ሙከራ በተደረገ ጥናት በድምፅ አካባቢያቸውን መለየት የሚችሉ ዓይነሥውራን አንዴ ወይም ሁለቴ ብቻ ድምፅ በማውጣት ከፊታቸው ያለን እቃ ምንነት ማወቅ እንደሚችሉና ዕቃው ከኋላ ወይም ወደ ጎን ሆኖ ከተመቀመጠ ግን ከ10 እስከ 12 ጊዜ ያህል ድምፆችን ማውጣተ እንደሚጠብቅባቸው ማወቅ ችለናል ብለዋል፡፡

በዚህ አካበቢን የመለየት ስልት የተካኑትን ማጥናት ስልቱን ለሌሎች ዓይነሥውራን ለማስተማር ይረዳል ተብሏል፡፡

በዚህ በድምፅ አካባቢን ለይቶ በመንቀሳቀስ ከተካኑት ዓይነሥውራን መካከል አንዱ የሆነውና በጉዳዩም ዙሪያ በመላው ዓለም የሚታወቀው ዳንዔል ኪሽ፣ “ስልቱን መካን ለዓይነሥውራን በተወሰነ መልኩ ዓይንን ከፍቶ ማየት እንደመቻል ነው” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል፡፡

ሌላው ሰሞኑን የተሰማ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ ደግሞ ጨረቃ አራተኛው ትውልድ የሚባለው የ4ጂ ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት ልታገኝ ነው ይላል፡፡

ጨረቃ ላይ ፈጣኑን ኢንተርኔት ለመዘርጋት ቮዳፎን እና ኖኪያ ኩባንያዎች ደፋ ቀና እያሉ ነው ተብሏል፡፡

ፈጣኑ ኢንተርኔት የሚዘረጋው ደግሞ ወደዚያ ለምርምር ለሚያመሩት ሁለት የምርምር ሮቦቶች ሲሆን ሮቦቶቹ በፈጣኑ ኢንተርኔት አማካኝነት ጥራት ያላቸው ቪዲዮዎችን ከጨረቃ እየቀረፁ ወደ ምድር ለመላክ ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡

ፕሮጀክቱ እ.ጎ.አ በ2019 ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል::

ምንጭ:- የሸገር FM 102.1 ሬዲዮ

 

Advertisement