አዲስ የፀረ-ተህዋስ ዝርያ በአፈር ውስጥ ተገኘ – New Species of Antibodies Found in Soil

                             

እነዚህ የተፈጥሮ ስብጥሮች ከባድ የሚባሉ ኢንፌክሽኖችን የማከም አቅም ያላቸው ናቸው ሲሉ በሮክፌለር ዩኒቨርሲቲ ያለው ቡድን ተስፋውን ገልጿል።

የተደረጉት ምርምሮች ማሊሲዲንዝ የተሰኙት ስብጥሮች ባሉት የፀረ-ተህዋስ መድሃኒቶች የማይበገሩትን እንደ ኤምአርኤስኤ ያሉ የተለያዩ በባክቴሪያ የሚመጡ በሸታዎችን የማስወገድ አቅም አላቸው።

ባለሙያዎች ‘ኔቸር ማይክሮባዮሎጂ’ በተሰኘው የድረ-ገጽ መጽሔት ላይ እንደገለጹት ፀረ-ተህዋስን በመፈለጉ ሩጫ ላይ ተስፋ እንዳለ ነው።

መድሃኒት የማይበግራቸው በሽታዎች የዓለማችንን አጠቃላይ ጤና የሚያውኩ ናቸው።

እነዚህ በሽታዎች በየዓመቱ እስከ 700 ሺህ ሰዎችን ይገላሉ ስለዚህም ነው አዳዲስ መፍትሔዎች በአስቸኳይ የሚያስፈልጉት።

ከአፈር መድሃኒት

አፈር በሚልዮን የሚቆጠሩና የተለያዩ ለዓይን የማይታዩ (ማይክሮ ኦርጋኒዝም) ፀረ-ተህዋስን ጨምሮ በርካታ ስብጥሮችን ይይዛል።

በኒው ዮርክ የሚገኘው የሮክፌለር ዩኒቨርሲቲው የዶ/ር ሾን ብሬዲ ቡድን ደግሞ እነዚህን ሲፈልግ ቆይቷል።

የጂን ማከታተያ (ጂን ሲክወንሲንግ) በመባል የሚታወቀውን ዘዴ በመጠቀም በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከ1000 የአፈር ናሙናዎች በላይ ሲያጠኑ ቆይተዋል።

ማላሲዲንዝ የተሰኘውን ደግሞ በብዙ ናሙናዎች ላይ አግኝተውታል። ይህም በጣም አስፈላጊ መሆኑን እንዲገናዘቡ አድርጓቸዋል።

ለአይጦች የፀረ-ተህዋሱን ስብጥርን ከሰጡ በኋላ በቆዳቸው ላይ ባለ ቁስል ላይ ያጋጠመን ኤምአርኤስኤ የተባለውንኢንፌክሽን ለማስወገድ ችለዋል።

ተመራማሪዎቹም መድሃኒቱ ለሰዎች ማከሚያ ይሆናል በሚል ተስፋ በትክክል መሥራት አለመሥራቱን ሲያጠኑ ቆይተዋል።

ዶ/ር ብሬዲ” ማላሲዲንዝን የመሰሉ መድሃኒቶችን ወደ ገበያ ለማምጣት መቼና እንዴት አንደሚሆን ለመናገር ይከብዳል” ብለዋል።

“ከግኝቱ እስከ ገበያ ድረስ ያለው ረዥምና ከባድ መንገድ ነው” ሲሉም አክለዋል።

በእንግሊዝ የፀረ-ተህዋስን ምርምር ፕሮፌሰር የሆኑት ኮሊን ጋርነር ኤምአርኤስኤን የመሰሉ በሽታዎችን ለማከም የሚችሉ መድሃኒቶችን ማግኘቱ በእራሱ ጥሩ ዜና ቢሆንም እንኳን፤ ከባዱን ችግር ለመቅረፍ አያስችልም ብለዋል።

“የእኛ ስጋት እነዚህ ባክቴሪዎችን ለማስወገድ ከባድ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ፀረ-ተህዋስ መድሃኒቶችን የመቋቋም አቅማቸውን መጨመሩ ነው” በማለትም ቀጥለዋል።

“እንደ ኤምአርኤስኤ ያሉ ባክቴሪያዎች ኒሞንያ ያስከትላሉ በተጨማሪም የደምና የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽኖችንም ሊያመጡ ይችላሉ። እነዚህንም ለማስወገድ አዲስ የፀረ-ተህዋስ ዝርያ ያስፈልገናል” ብለዋል።

Advertisement