ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብን 19 በመቶ ድርሻ አገኘች – Ethiopia Acquires 19% Stake in Somaliland Berbera Port

                                 

ኢትዮጵያ በሶማሌላንድ በርበራ ወደብ 19 በመቶ ድርሻ መያዟን ወደቡን የሚያስተዳድረው የዱባዩ ዲ ፒ ወርልድ ኩባንያ ገለፀ።

ኩባንያው ዛሬ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ፥ በወደቡ ዲ ፒ ወርልድ ራሱ 51 በመቶ፣ ሶማሌላንድ 30 በመቶ እና ቀሪውን 19 በመቶ ድርሻ ኢትዮጵያ እንደሚይዙ አስታውቋል።

በስምምንቱ መሰረት ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብን ለገቢ እና ወጪ ንግዷ ለመጠቀም የሚያስችላትን መሰረተ ልማት እንደምታለማ በመግለጫው ላይ ተመልክቷል።

የዲ ፒ ወርልድ ግሩፕ ሊቀመንበር እና ዋና ስራ አስፈፃሚ ሱልጣን አህመድ ቢን ሱለይም ከኢትዮጵያ ጋር ኩባንያቸው በአጋርነት መስራቱ የሀገሪቱ መንግስት ያወጣቸው አስደናቂ ያሉት የልማት እቅድ እንዲሳካ እንድናግዝ እድል ይሰጠናል ብለዋል።

የአካባቢው ኢኮኖሚ በፍጥነት እያደገ እንደመሆኑ ይህንን አድገት የሚመጥን የወደብ አገልግሎት እንደሚያስፈልግ በመግለፅ፥ የበርበራ ወደብ ልማት የጅቡቲን ወደብ በመደገፍ ተጨማሪ የባህር በር እንደሚሆን ገልፀዋል።

የኢፌዴሪ የትራንስፖርት ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ኢትዮጵያ ተከታታይ ድርድርን ከሶማሌላንድ እና ከዲፒ ወርልድ ግሩፕ ጋር ካካሄደች በኋላ በበርበራ ወደብ 19 በመቶ ድርሻ ማግኘቷን ገልፀዋል።

ይህም እያደጉ የመጡት ኢኮኖሚዋ እና የህዝብ ቁጥሯ ላሳደጉት የገቢ እና ወጪ ንግድ ተጨማሪ የባህር በር እንድታገኝ አስችሏታል ብለዋል።

በመሰረተ ልማቱም ኢትዮጵያ መሳተፏ ለሶማሌላንድ ህዝብና ኢኮኖሚ ልማት እና ተጨማሪ አድል ይዞ እንደሚመጣም ነው ያመለከቱት።

ኢትዮጵያ የጅቡቲ ወደብ ኮሪደርንም ማልማቷን ትቀጥላለች ያሉት አቶ አህመድ፥ በተጨማሪም ሌሎች የወደብ እና የሎጀስቲክ ኮሪደሮችንም ለመጠቀም ጥረቷን እንደምትቀጥል አስታውቀዋል

ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብ ተጠቃሚነቷን ለማሳደግ የሚያስችል ስምምነትን 2008 ላይ ነው ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው።

ሀገሪቱ 30 በመቶ የሚሆነው የወጪ ንግዷ በበርበራ ወደብ በኩል እንዲወጣ ብትፈልግም እስካሁን 97 በመቶ የሚሆነው የወጪ ንግዷ በጂቡቲ ወደብ በኩል ነው እየተካሄደ ያለው።

Advertisement