የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ሽልማትን አገኘ – Ethiopian Airlines Jot International Award

                                

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ2017 “ፈጣን እድገት ላይ የሚገኝ ዓለም አቀፍ እቃ ጫኝ አየር መንገድ” በመባል በህንድ ዓለም ዓቀፍ ጉባዔ ላይ ሽልማቱን ተረከበ።

ሽልማቱን ያገኘው የካቲት 14 ቀን 2010 ዓ.ም በሕንድ ሙምባይ ከተማ ለሰባተኛ ጊዜ በተካሄደው “የኤር ካርጎ ኢንዲያ” ዓለም አቀፍ ጉባዔና አውደ ርዕይ ላይ ነው።

አየር መንገዱ አሸናፊ ሊሆን የበቃው የስታት ታይምስ ድረገጽ አንባቢዎች በኢንተርኔት በሰጡት ድምጽ አማካኝነት መሆኑ ተገልጿል።

ይህ ሽልማት በየሁለት ዓመቱ ለአሸናፊዎች የሚበረከት ሲሆን፥ በካርጎ አገልግሎት ከፍተኛ ለውጥና በዘርፉ ኢንዱስትሪ የደንበኞችን ፍላጎት ለማሟላት በዓለም አቀፍ ደረጃ መሪ የሚባሉ የፈጠራ ሀሳቦች ወደ ኢንዱሰትሪው ለሚያመጡ አየር መንገዶች እውቅና ይሰጣል።

የኢትዮጵያ የካርጎና ሎጂስቲክስ አገልግሎት የስራ ክፍል በአሁኑ ወቅት በአምስት አህጉራት በዓመት 400 ሺህ ቶን ካርጎ በማጓጓዝ የአፍሪካን የንግድና የኢኮኖሚ እድገት እያገዘ ነው ተብሏል።

አየር መንገዱ በአምስት አህጉራት 110 የካርጎ መዳረሻዎችም ያሉት ሲሆን፥ በ2025 ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ገበያና ደንበኛ ተኮር እንዲሁም የፖስታ መልዕክቶች በማጓጓዝ በአፍሪካ ተወዳዳሪና መሪ የካርጎ አየር መንገድ የመሆን ራዕይ ሰንቆ እየሰራ ነው።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement