ካሊፎርኒያ አሽከርካሪ አልባ ተሽከርካሪዎችን በጎዳናዎች ላይ ልትሞክር ነው – California Green Lights Fully Driverless Cars For Testing on Public Roads

                                        

ካሊፎርኒያ አሽከርካሪ አልባ ተሽከርካሪዎችን ከመጭው ሚያዚያ ወር ጀምሮ በጎዳናዎች ላይ ልትሞክር ነው።

የተሽከርካሪዎቹ ሙከራ ያለምንም አሽከርካሪ ብቻ የሚደረግ ሲሆን፥ ኩባንያዎች ለዚህ የሚያገለግሉ ተሽከርካሪዎችን የማዘጋጀት ሃላፊነት አለባቸው ተብሏል።

ከመጭው ሚያዚያ ወር በሚጀምረው ሙከራ በመላው የካሊፎርኒያ ግዛት ጥቅም ላይ ለመዋል የሚቀርቡ አሽከርካሪ አልባ ተሽከርካሪዎች ያለ አሽከርካሪ የመንገድ ላይ ሙከራቸውን ያደርጋሉ።

ይህን ሙከራ ማድረግ የፈለጉ አሽከርካሪ አምራቾች ታዲያ ከግዛቲቱ የተሽከርካሪ መምሪያ ክፍል ፈቃድ ማግኘት ይኖርባቸዋል።

የግዛቲቱ የተሽከርካሪ መምሪያ ክፍል ሁሉም ተሽከርካሪዎች ያለ አሽከርካሪ በጎዳና ላይ ሙከራቸውን እንዲያደርጉ የሚያደርግ መመሪያ ትናንት አድቋል።

እስከዛሬ ድረስ አዲስ የሚሰሩ አሽከርካሪ አልባ ተሽከርካሪዎች ራሳቸውን ችለው የመንገድ ላይ ሙከራ ቢያደርጉም፥ ሁኔታውን በቅርበት የሚከታተል አሽከርካሪ ግን እንዲኖር ይደረግ ነበር።

በአዲሱ መመሪያ መሰረት ግን ከፈረንጆቹ ሚያዚያ 2 ጀምሮ ሁሉም አሽከርካሪ አልባ ተሽከርካሪዎች ያለ አሽከርካሪ እንዲሞከሩ ይደረጋል ነው የተባለው።

ተሽከርካሪ አምራቾችም በተሽከርካሪውና በተቆጣጣሪው መካከል መግባባት ይኖር ዘንድ የሚያስችል መገናኛ ቴክኖሎጅን ማመቻቸት ይጠበቅባቸዋል።

ከዚህ ባለፈም ተሽከርካሪዎች በእንቅስቃሴ ወቅት በመረጃ መረብ ጠላፊዎች አማካኝነት አደጋ እንዳያስተናግዱ መከላከልም የእነርሱ ድርሻ ይሆናል።

በሙከራ ወቅት የሚያጋጥምን ማንኛውንም ሁኔታ ማሳወቅና ማስረዳትም ሌላው ሃላፊነት ይሆናል።

አሽከርካሪ አልባ ተሽከርካሪዎችን መገጣጠም አሁን በአውቶሞቢል ኢንዱስትሪው ውስጥ ትልቁን ድርሻ እየያዘ ነው።

ኩባንያዎችም መሰል ቴክኖሎጅዎችን በመጠቀም ሙከራዎችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

የመረጃ ማፈላለጊያ ገጽ የሆነው ጎግል አሽከርካሪ አልባ ተሽከርካሪዎችን ከሶስት ሚሊየን ማይል በላይ ሲሞክር፥ ኡበር ደግሞ ከአንድ ሚሊየን ማይል በላይ በጎዳና ላይ ሞክሯል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement