በመዲናዋ ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ የተመደበው ተዘዋዋሪ ፈንድ በሚፈለገው ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም

                                                                           

በአዲስ አበባ ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ የተመደበው ተዘዋዋሪ ፈንድ በሚፈለገው ደረጃ ጥቅም ላይ እየዋለ አለመሆኑን የአዲስ አበባ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ገለፀ።

ከአመት በፊት በሃገር አቀፍ ደረጃ ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ከተመደበው 10 በሊየን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ፥ አዲስ አበባም የእድሉ ተጠቃሚ እንድትሆን የ2 ነጥብ አራት ቢሊየን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ፀድቆላታል። ፈንዱ ጥቅም ላይ መዋል ከጀመረም አንድ አመት አስቆጥሯል።

በእነዚህ ጊዜያትም ከዚህ ቀደም ስራ ያልነበራቸዉ እና በራሳቸዉ ተንቀሳቅሰው የተሻለ ገቢን ለማግኘት እና ለሌሎችም የስራ እድል ለመፍጠር ፍላጎት ያላቸው ወጣቶች በተለያዩ ዘርፎች በመደራጀት ከፈንዱ ተበድረው ተጠቃሚ ሆነዋል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ባደረገው የመስክ ምልከታ ከዚህ ቀደም ተዘዋዋሪ ፈንዱ ከመቅረቡ በፊት በየክፍለ ከተማቸው ብድር በመውሰድ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙና ስራቸዉን ለማሳደግ የፈለጉም ከተዘዋዋሪ ፈንዱ ተጠቃሚ ለመሆን ዝግጅት ላይ የሚገኙ ኢንተርፕራይዞችንም አግኝቷል።

በሌላ በኩል በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ተመርቀዉ እና የመስራት ፍላጎቱ እያላቸው እድሉን ሳያገኙ ከቤት የዋሉ ወጣቶችም አሉ። 

በዚህም ከአዲስ አበባ አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው፥ በብድር ገንዘቡ የስራ እድል ለመፍጠር በመጀመሪያ ዙር ለመዲናዋ ከተፈቀደው 419 ሚሊዮን ብር በአንድ አመት ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለው 67 ሚሊዮን ብር ብቻ ነው። 

በብድር ገንዘቡ ተጠቃሚ ለመሆንም 10 ሆኖ መደራጀት እንደ መስፈርት የተቀመጠ ሲሆን፥ ባለፈው አንድ አመት ማደራጀት የተቻለው የኢንተርፕራይዝ ቁጥርም ከ385 አልበለጠም።

በኢንተርፕራይዙ የስራ እድል ፈጠራ ቡደን መሪ አቶ ነብዩ ውድነህ እንደተናገሩት፥ ከ57 ሺህ በላይ ኢንተርፕራይዞችን ለማደራጀት ከተቀመጠው እቅድ አንፃር ሲታይ አፈፃፀሙ ዝቅተኛ ነው። 

በተዘዋዋሪ ፈንድ አሰጣጥ ላይ የግንዛቤ እጥረት፣ የወጣቶች ስራ ቅጥር ላይ የማተኮር እና በርካታ የስራ እድል የማይፈጥሩ የስራ መስኮች ላይ ለመሰማራት ያለው ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ለአፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆን እንደ ምክንያት ይጠቅሳሉ።

በተጨማሪም ለስራ እድል ፈጠራው ትኩረት በተሰጠው የማምረቻ እና የከተማ ግብርና ላይ ለመሰማራት የወጣቶቹ ፍላጎት አነስተኛ ነው ብለዋል።

ይህን ችግር ለመፍታትም ከፍተኛ የግንዛቤ ማሳደግ ስራ መሰራት ይኖርበታል ነው ያሉት።

ለዚህም በዚህ አመት የኢንተርፕራይዞችን ቁጥር ለማሳደግ እንዲቻል ከ30 ሺህ በላይ ወጣቶችን በቤቶች ልማት፣ ከ14 ሺህ በላይ ወጣቶችንም በተለያዩ የማምረቻ ዘርፎች ለማሰማራት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ሃላፊው ጠቁመዋል።

ከዚህም ባለፈ በቀጥታ የስራ እድል ፈጠራ እስከ 103 ሺህ ወጣቶች ተጠቃሚ ለማድረግ ከ21 የመንግስት ተቋማት ጋር እየተሰራ ነው ተብሏል።

የማምረቻ ቦታዎች እጥረትን ለመቅረፍም በዚህ ዓመት ከ700 በላይ የማምረቻ ሼዶች ግምባታ ይከናወናል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

Advertisement