ዓይኖች በእነዚህ ሰዎች ላይ ናቸው

                                   

ያሳለፍነው ሳምንት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታን ይዞ አልፏል። በመጀመሪያዎች የሳምንቱ ቀናት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ጠንካራ የሚባል የቤት ውስጥ መቀመጥ አድማ ተከናወነ። በቀጣዮቹ ቀናት በሽብር ወንጀል የተከሰሱና ተፈርዶባቸው የነበሩ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችም ተፈቱ።

በሳምንቱ መገባደጃ ላይ ደግሞ ጠቅላይ ሚንስትሩ የስልጣን ልልቀቅ ጥያቄያቸውን ማቅረብ ተከትሎም አርብ ማምሻውን ደግሞ አነጋጋሪ የሆነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ።

ከዚህ ሁሉ በኋላ ተሰናባቹን ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ማን ይተካቸዋል የሚለው መነጋገሪያ ሆኗል። በርካቶችም በማህበራዊ ድረ-ገፆች እና መገናኛ ብዙሃን ላይ ጠቅላይ ሚንስትሩን ሊተኳቸው ይችላሉ የሚሏቸውን ሰዎች ሲጠቅሱ ቆይተዋል።

የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 73 ንዑስ አንቀጽ 1 ስለ ጠቅላይ ሚንስትሩ አሰያየም በግልጽ እንደሚያትተው፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መካከል ይመረጣል። ሊመረጥ የታሰበው ግለሰብ ግን የምክር ቤቱ አባል ካልሆነ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ቦርድ ሟሟያ ምርጫ እንዲያካሂድ ከጠየቀ በኋላ፤ ዕጩውን ግለሰብ በሟሟያ ምርጫው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆኖ መመረጥ አለበት።

ማሟያ ምርጫ ማለት በይውረድልን ወይም በማንኛውም ምክንያት በየደረጃው የሚገኙ የተጓደሉ የምክር ቤት አባላት መቀመጫዎችን ለማሟላት የሚካሄድ ምርጫ ማለት ነው።

ጠቅላይ ሚንስትሩን ለመተካት የሚታጨው ግለሰብ ግን የምክር ቤት አባል ከሆነ በተለመደው የኢህአዴግ አሰራር መሰረት፤ የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ተካሂዶ ሊቀመንበሩን ከመረጠ በኋላ፤ ሊቀመንበሩን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ በጠቅላይ ሚንስትርነት እንዲሰየም ይደረጋል።

ሰሞኑን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እና በማህበራዊ ድረ ገፆች ላይ በተደጋጋሚ ስማቸው እየተጠቀሰ የሚገኙት ሰዎች የሚከተሉት ናቸው። እነዚህ ግለሰቦች እነማን ናቸው?

አጭር የሕይወት ታሪካቸውን እንደሚከተለው ቀርቧል። ስማቸው የተዘረዘረው በእንግሊዝኛ የፊደላት ቅደም ተከተል መሰረት ነው።

ክተር አብይ አህመድ

ዶክተር አብይ አህመድ በአጋሮ ከተማ የተወለዱ ሲሆን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ አግኝተዋል።

ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ሰርተዋል።

በግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ እና በሊደርሺፕ ተቋም ደግሞ የሥራ አመራር ሳይንስ አጥንተዋል። እንዲሁም አሽላንድ ዩኒቨርሲቲ በንግድ አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪ ያገኙ ሲሆን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሰላም እና ደህንነት ጥናት ፒኤችዲ አላቸው።

በመጀመሪያ 40ዎቹ የሚገኙት ዶክተር አብይ ኦህዴድን የተቀላቀሉት በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነው። ከፖለቲካ ተሳትፏቸው በተጨማሪ በወታደራዊ ጉዳዮች ሰፊ ተሳትፎ የነበራቸው ሲሆን የሌተናል ኮሎኔል ማዕረግ አላቸው።

በተባበሩት መንግሥታት የስላም ማስከበር ተልዕኮን ለማስፈጸም ሩዋንዳ ዘምተዋል።

ከ2000 እሰከ 2003 የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ መስራች እና ዳይሬክተር በመሆነ አገልግለዋል። ከዚያም የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚንስትር በመሆን ሰርተዋል።

ከ2002 ጀምሮ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩ ሲሆን፤ ከ2007 ጀምሮ ደግሞ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ከዚህ በተጨማሪ ላለፉት ሦስት ዓመታት የኢህአዴግ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ። ዶክተር አብይ የኦህዴድ ማዕከላዊ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ናቸው።

ዶክተር አብይ በአሁኑ ጊዜ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ናቸው።

ክተር ደብረዮን ገብረ ሚካኤል

በትግራይ ሽረ ወረዳ ነው የተወለዱት። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ከተቀላቀሉ በኋላ ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ትጥቅ ትግል ገብተዋል።

በትጥቅ ትግል ወቅት ወደ ጣልያን አገር በመሄድ በመገናኛ ቴክኖሎጂ ስልጠና የወሰዱ ሲሆን፤ በ1972 ዓ.ም የህወሓት ሬድዮ ጣብያ ድምፂ ወያነን አቋቁመዋል።

ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ሲወጣ የደህንነት መ/ቤቱን ይመሩ የነበሩት የአቶ ክንፈ ገብረ መድህን ምክትል ሆነውም አገልግለዋል።

ቀደም ሲል ያቋረጡትን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ተከታትለው የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ተቀብለዋል።

እንዲሁም ደግሞ የዶክትሬት ድግሪያቸውን ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ለንደን አግኝተዋል።

ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ የኢንፎርሜሽንና ኮምዩኒኬሽን ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፤ በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ማዕረግ የክላስተር አስተባባሪ ሆነውም ሰርተዋል።

በአሁን ሰዓት የህወሓት ሊቀመንበር፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳደርነት የትግራይ ክልልን እንዲሁም የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ሚንስትር ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።

ዶክተር ደብረፅዮን በአሁኑ ጊዜ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ናቸው።

ደመቀ መኮንን

በ1980 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በባዮሎጂ ትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል። ከዚያም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በግጭት አፈታት አጠናቀዋል።

በ1980ዎቹ መጀመሪያ ኢህአዴግን የተቀላቀሉት አቶ ደመቀ፤ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የአማራ ክልል ምክር ቤት ተመራጭ ሆነው ነበር።

በ1997 የአማራ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ሆነው የተመረጡ ሲሆን፤ በቀጣዩም ዓመት የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆነው ተመርጠዋል።

አቶ ደመቀ መኮንን የብአዴን ሊቀመንበር ሲሆኑ በኀዳር 2005 ዓ.ም የኢህአዴግ ምክትል ሊቀምንበር ሆነው ከተመረጡበት ጊዜ ጀምሮ በምክትል ጠቅላይ ሚንስትርነት እያገለገሉ ይገኛሉ።

የቀድሞው መምህር ወደዚህ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት የትምህርት ሚንስትር ሆነው አገልግለዋል።

አቶ ደመቀ መኮንን በአሁኑ ጊዜ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ናቸው።

አቶ ለማ መገርሳ

አቶ ለማ መገርሳ የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ሊቀመንበር እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳደር በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።

በአርባዎቹ መጨረሻ ላይ እንደሚገኙ የሚነገርላቸው አቶ ለማ፤ ትውልድ እና እድገታቸው ምስራቅ ወለጋ ነው።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የመጀመሪያ ዲግሪ ያገኙ ሲሆን በተመሳሳይ የትምህርት ዘርፍ ሁለተኛ ዲግሪያቸውንም ከዚያው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል።

ከሁለት ዓመታት በፊት በኦሮሚያ ህዝባዊ ተቃውሞ በበረታበት ወቅት ነበር የኦህዴድ ሊቀመንበር እና የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ሆነው የተመረጡት።

አቶ ለማ በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ኦህዴድን የተቀላቀሉ ሲሆን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ከመሆናቸው በፊት የክልሉ ምክር ቤት – የጨፌ አፈጉባኤ ነበሩ።

አቶ ለማ መገርሳ የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት-ጨፌ አባል ሲሆኑ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ግን አይደሉም።

ክተር ወርቅነህ ገበየ

ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የኦህዴድ ምክትል ሊቀመንበር እና የኢፌዴሪ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ናቸው።

የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በፖለቲካል ሳይንስ እና በውጪ ግንኙነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አጠናቀዋል።

ከሁለት ዓመታት በፊት ከደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ በፖሊስ ሳይንስ ዶክትሬት ዲግሪን አግኝተዋል።

1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ የተወለዱት ዶክተር ወርቅነህ ለረጅም ዓመታት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሸነር በመሆን አገልግለዋል።

ከ2004 ጀምሮ የትራንስፖርት ሚንስትር በመሆን ለአራት ዓመታት ሰርተዋል።

ከ1980ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ የኦህዴድ አባል የነበሩት ዶክተር ወርቅነህ፤ ከ2004 ጀምሮ የኦህዴድ እና የኢህዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ናቸው።

ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ምክር ቤት አባል እንጂ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አይደሉም።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement