ትራምፕ ተሻሽለው የተሰሩ መሳሪያዎች ላይ እገዳ እንዲጣል አዘዙ

                                                      

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ባምፕ ስቶክ” የሚባሉትን የመሳሪያ አይነቶች ለማገድ ትዕዛዝ ፈረሙ።

ባለፈው አመት ላስቬጋስ በነበረ ኮንሰርት 58 ሰዎችን የገደለው ተኳሽ የተጠቀመበትም ተመሳሳይ መሳሪያ ነው።

በደቂቃ ውስጥ ከመቶዎች ጊዜ በላይ መተኮስ እንደሚያስችል ተዘግቧል።

በዋይት ሀውስ ባደረጉት ንግግር የፍትህ ክፍሉ እነዚህ መሳሪያዎች ህገወጥ ለማድረግ የሚያስችል ህግም እንዲያረቁ አዘዋል።

ይህ የመሳሪያ ቁጥጥር ክርክር ባለፈው ሳምንት በፍሎሪዳ ለ17 ሰዎች ህይወት መቀጠፍ ምክንያት የሆነው ተኩስ ከተፈጠረ በኋላ እንደ አዲስ መወያያ ርዕስም ሆኗል።

በማርጆሪ ስቶንማን ዳግላስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በደረሰው ጭፍጨፋ የተጎዱ ተማሪዎችና ቤተሰቦች በመዲናዋ ታልሀሲ ዛሬ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እቅድ ይዘዋል።

አንዳንዶቹ ተማሪዎች ማክሰኞ እለት ህግ አስፈፃሚዎች መሳሪያዎችና መፅሄቶችን እንዲከለክል የረቀቀውን ህግ ውድቅ ሲደረግም በጊዜው ተገኝተው ታዛቢ ሆነዋል።

ነገር ግን በአጠቃላይ በተወሰነ መልኩ የመሳሪያ ቁጥጥር ማድረግ የሚያስችል ክልከላዎች እንደሚቀመጡ ተዘግቧል።

ወደ 100 የሚሆኑ ተማሪዎች በሶስት አውቶብሶች ተጭነው የሰባት ሰዓት ጉዞ በማድረግ ቦታው ላይ ደርሰዋል።

ለአብዛኛዎቹ ተማሪዎች ታልሀሲ ሲገኙ የመጀመሪያቸው ሲሆን በሀገራዊ ሁኔታ ህግ አውጭዎችን መሞገትም የማይታሰብ ሁኔታ ነበር።

በሀገሪቱ እንቅስቃሴ ጀማሪዎች መሆናቸውም በተማሪዎቹ ደስታን እንደፈጠረም ተገልጿል።

“ወደ መዲናዋ ተጉዘን የመጣነው አብረናቸው ያደግናቸውና የምናቃቸው ሰዎች ሲሞቱ ዝም ብለን አንመለከትም ብለን ነው” በማለት ጁሊያ ሳልሞን የተባለች የ18 ዓመት ልጅ ተናግራለች።

እነዚህ ተማሪዎች ፖለቲከኞቹ እንዴት እንዲቀበሏቸው ይፈልጋሉ? “በእውነቱ ከሆነ ያለንን ቁርጠኝነት ከፊታችን ሲረዱት የሚገረሙ ይመስለኛል። አሁን የምንታገለው ለዚህ ነው” በማለት የምትናገረው የ16 ዓመቷ ሬይን ቫላዴርስ ስትሆን “ፊታችንን አይተው የማንመለስበት ደረጃ ላይ እንደደረስን ያዩታል” ብላለች።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement