ኢትዮጵያ በጅቡቲ ከምትገነባቸው መናኸሪያዎች የአንዱ ሥራ 15 ከመቶ ደርሷል ተባለ

                              

ኢትዮጵያ ከውጭ አገር ለምታስገባቸው ግብዓቶች ቅልጥፍና ይረዳት ዘንድ በጅቡቲ የደረቅ ጭነት መናኸሪያ ግንባታ 15 በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ የፈሳሽ ጭነት መናኸሪያ ለመገንባት 20 ሚሊዮን ብር ቢመደብም የተሰጠው ቦታ ውዝግብ በማስነሳቱ ሥራውን ለመጀመር መቸገሩን የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
የባለሥልጣኑ የኮርፖሬት ሥራዎች ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ በቀለ እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት በጅቡቲ በመገንባት ላይ ያለው የከባድ ጭነት መናኸሪያ በቻይና ሥራ ተቋራጭ ኩባንያ እየተከናወነ ሲሆን፤ በተያዘለት የ94 ሚሊዮን ብር በጀት ግንባታው 15 ከመቶ ደርሷል፡፡ የአፈር ናሙና ጥናት በመከናወኑም አስፋልት የማንጠፍ ሥራውን ለማከናወን በቅርቡ ሥራ ይጀመራል፡፡
በጅቡቲ የሚገነባውና በዚህ ዓመት 40 ሚሊዮን ብር በጀት የተያዘለት በጠጠር የሚገነባው ሁለተኛው መናኸሪያ በቦታው ላይ 30 ከመቶ የሚሆነው መሬት ‹‹ኳሪ›› ድንጋይ በመገኘቱ ተቋራጩ ለድንጋይ ማውጫ 1ሺ400 ብር በመጠየቁና በሜትር ኪዩብ 560 ብር እንደሚከፈለው ቢገለፅለት ባለመስማማቱ ሥራው መቋረጡን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በጅቡቲ የሚገነባው የፈሳሽ ጭነት መናኸሪያ ሥራን ለማፋጠን ቢታቀድም የጅቡቲ መንግሥት ቀደም ሲል ለግንባታው የሰጠው ቦታ ውዝግብ ስለፈጠረ በባለሥልጣኑ የማግባባት አቅም ብቻ መፍትሄ ማምጣት አዳጋች መሆኑን፤ በዚህ ምክንያትም ዲዛይን ለማሠራት ጨረታ ማውጣት እንዳልተቻለ ገልፀው፤ በጅቡቲ ኢትዮጵያ አምባሳደር መፍትሄ ለመስጠት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ሊሳካ ባለመቻሉ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ምንጭ፦አዲስ ዘመን

Advertisement