NEWS: በሻሸመኔ እስር ቤት በተነሳ እሳት የአንድ ሰው ሕይወት አለፈ

                                              

ዛሬ ጠዋት በሻሸመኔ በሚገኘው እስር ቤት ላይ በደረሰው የእሳት ቃጠሎ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን፣ ሶስት ሰዎች መቁሰላቸውንና የእስረኞች ማደሪያ የነበረው ቤት በቃጠሎ መውደሙን የማረሚያ ቤቱ ኃላፊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የእስር ቤቱ ኃላፊ የሆኑት ከፍተኛ ኢንስፔክተር ፈይሳ ትክሴ እንደተናገሩት እሳቱ ከተነሳ በኋላ ለማምለጥ የሞከረ አንድ ታራሚም በጥይት ተገድሏል።

ከማለዳው አንድ ሰአት ተኩል ላይ የተነሳው ቃጠሎ ምክንያት “እስረኞቹ ሆን ብለው የኤሌትሪክ ገመዶችን በማያያዝ ያስጀመሩት ነው”ብለዋል።

በዚህ ማረሚያ ቤት ውስጥ በአጠቃላይ ወደ 2000 የሚጠጉ እስረኞች የሚገኙ ሲሆን ይጠቀሙበት ከነበረው አምስት ብሎኮች ሶስቱ በቃጠሎው ሙሉ በሙሉ መውደሙንም ከፍተኛ ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰአት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመሆን እሳቱ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር መዋሉን እና አሁን ለእስረኞቹ ማደሪያ በማመቻቸት ላይ መሆናቸውን ኃላፊው ጨምረው ገልፀዋል።

ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል የአይን እማኝ ለቢቢሲ እንደተናገረው የማረሚያ ቤቱ አካባቢ በመካለከያ እና በኦሮሚያ ፖሊስ ጥበቃ እየተደረገለት ይገኛል።

እንዲሁም ማለዳ ተዘግቶ የነበረው ከሻሸመኔ ወደ ሐዋሳ የሚወስደው ዋና መንገድ አሁን ተከፍቶ አገልግሎት መጀመሩን እና ከተማዋ በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ መሆኗንም ይህው የአይን እማኝ ተናግሯል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement