NEWS: ጃኮብ ዙማ ስልጣን ለቀቁ – President Jacob Zuma Resigns From Presidency

                                                     

ስልጣን አለቅም ብለው የነበሩት እምቢተኛው ዙማ ከራሳቸው ኤኤንሲ ፓርቲ ግፊት ሲበረታባቸው በመጨረሻ ስልጣን መልቀቅ ግድ ሆኖባቸዋል።

በቴሌቭዥን በተላለፈው ንግግራቸው ስልጣን መልቀቃቸውን ነገር ግን በፓርቲያቸው ውሳኔ እንደማይስማሙ ገልፀዋል።

ፓርቲያቸው ኤኤንሲ ለ75 ዓመቱ ዙማ ለምክትል ፕሬዝዳንቱ ሲሪል ራማፎሳ ስልጣን አስረክቡ የሚል ጥሪ ሲያደርግላቸው ቆይቷል።

እንደ አውሮፓውያኑ ከ2009 ጀምሮ ስልጣን ላይ የነበሩት ዙማ በርካታ የሙስና ውንጀላዎች ቀርበውባቸዋል።

ከዙማ ጋር ቅርብ ግንኙነት አለው የተባለው የሃያሉ ጉፕታ ቤተሰብ የጆሃንስበርግ መኖሪያ ትናንት በፖሊስ ቀጥጥር ስር ውሎ ነበር።

ዙማ የስልጣን ለቅቄያለሁ ንግግራቸውን የጀመሩት ለመቀለድ በመሞከርና ንግግራቸውን ለመታደም የተገኙ ጋዜጠኞችን ጥያቄ በመጠየቅ ነበር።

ከዚያም ዙማ ላለፉት ዓመታት አብረዋቸው የሰሩ ሰዎችን በማመስገን በፓርቲያቸው ኤኤንሲ ውስጥ የተፈጠረው መከፋፈል ስልጣን የመልቀቅ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ እንዳደረጋቸው ተናገሩ።

“በእኔ ስም ምንም አይነት ህይወት መጥፋት የለበትም።በእኔ ምክንያትም ኤኤንሲ ውስጥ መከፋፈል እንዲኖር አልፈልግም።ስለዚህም ስልጣን የመልቀቅ ውሳኔ ላይ ደርሻለው” ብለዋል ዙማ

በመቀጠልም ምንም እንኳን በፓርቲያቸው የስልጣን ልቀቁ ውሳኔ ባይስማሙም ሁሌም ስርዓት የሚያከብር የፓርቲው አባል መሆናቸውን ገልፀዋል።

በመጨረሻም “ስልጣን ብለቅም ህይወቴን ሙሉ ያገለገልኩትን የደቡብ አፍሪካ ህዝብና ፓርቲዬ ኤኤንሲን ማገልገሌን እቀጥላለሁ።”ብለዋል ዙማ።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement