“በሰላማዊ ትግል እስከመጨረሻው በፅናት እንታገላለን” እስክንድር ነጋ – “We Will Be Fighting Hard In Consistency Until The End” Eskinder Said

                                                              

ታዋቂው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከሰባት ዓመታት እስር ቆይታ በኋላ ትናንትና ነፃ ወጥቷል።

ብዙዎች በከፍተኛ ደስታ ተሞልተው የተቀበሉት ሲሆን እርሱም የተሰማውን ደስታ ለቢቢሲ ገልጿል።

“በመፈታቴ በጣም ደስተኛ ነኝ ከሁሉ በፊት ኃያሉን እግዚአብሔር አመሰግናለሁ እንድፈታ እስከመጨረሻ ድረስ ለታገለልኝ የኢትዮጵያ ህዝብን ማመስገን እፈልጋለሁ።” ብሏል።

በተደጋጋሚ ለእስር የተዳረገው እስክንድር ኢትዮጲስ የሚባል ጋዜጣም ባለቤት ነበር። የሰርካለም ማተሚያ ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ የነበረ ሲሆን በስሩም አስኳል፣ ሳተናውና ሚኒልክ የተባሉ ጋዜጦችንም ያሳትም ነበር።

የ1997 ምርጫ ቀውስንም ተከትሎ ጋዜጦቹ የተዘጉ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ በሀገር ክህደት ወንጀል ለእስር የበቃው እስክንድር በይቅርታ እንደተፈታ የሚታወስ ነው።

ከዚያም ከሰባት ዓመታት በፊት በሽብር ተከሶ ለ18 ዓመታት የተፈረደበት እስክንድር የኢትዮጵያ መንግሥት ‘አሸባሪ’ ብሎ ከፈረጀው ከግንቦት ሰባት ጋር ግንኙነት አለህ በሚል ነው።

የመጨረሻ ቀናት ስለነበረው የእስር ቤት ቆይታው የተናገረው እስክንድር መንግስት በይቅርታ ለመፍታት ካስቀመጠው የስልጠና እንዲሁም ከመፈረም ጋር የተያየዙ ናቸው።

“ፈርሙ አትፈርሙ የሚሉ ጉዳዮች ነበሩ። ስንታሰር ጀምሮ ይቅርታ እንደማንፈርም ተማምነን ነበር፤ በዛው ቃላችንን ጠብቀናል።” ብሏል

ባለመፈረማቸው ከእስር ቤት ላንለቀቅ እንችላለን የሚለው ፍራቻ እነደነበራቸው የሚናገረው እስክንድር ሆኖም አቶ በቀለ ገርባ በይቅርታ መውጣታቸውን ሲሰሙ “ያው እንደምንፈታ ገምተናል” ይላል።

ትናንት ከዕስር ከወጣም በኋላ በትግሉ እንደሚቀጥልም ተናግሯል።

“አሁንም በሰላማዊ ትግል ውስጥ እስከመጨረሻው ድረስ በፅናት እንታገላለን። በሰላማዊ መንገድ የዴሞክራሲውን ጥያቄ ባለን አቅም ሁሉ እናግዛለን። “

ጨምሮም “የወጣነው ትግሉን ከዳር ለማድረስ ነው።የህዝቡ ጥያቄ የእስረኞች መፈታት አይደለም፤ የዴሞክራሲ ጥያቄ እንዲመለስለት ነው፤ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ነው፤ ይህንን ትግል ደግሞ ባለኝ አቅም ሁሉ ከዚህ በፊት ካበረከትኩት አስተዋፅኦ በላይ አበረክታለሁ” ብሏል።

እስክንድር በእስር ላይ ሳለ እ.ኤ.አ የ2012ን የፔን/ባርባራ ጎልድስሚዝ የፅሁፍ ነፃነት እና እ.ኤ.አ የ2017 የዓለም አቀፍ የፕሬስ ተቋምን የዓለም የፕሬስ ነፃነት የጀግንነት ሽልማትን ተቀዳጅቷል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement