ኤለን ጆንሰን በአፍሪካ መልካም አስተዳደር ተሸላሚ ሆኑ – Ellen Johnson Sirleaf wins 2017 Ibrahim Prize for Achievement in African Leadership

                                                   

የላይቤሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ የሞ ኢብራሂም የአፍሪካ ሊደርሺፕ (የአፍሪካ አመራር) የ5 ሚሊየን ዶላር ሽልማት አሸነፉ።

ፕሬዚዳንቷ ባለፈው ወር ከስልጣን የወረዱ ሲሆን በ2006 ነበር የመጀመሪያዋ ሴት አፍሪካዊ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት።

ሀገሪቷ ከነበረችበት የእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ መልሶ በመገንባት እና የእርቁን ሂደት በመምራት ረገድ ውዳሴ ሲቀርብላቸው ነበር።

የሽልማት ኮሚቴው እንዳለው ፕሬዚዳንቷ ምንም እንኳ ሙስናን በመዋጋት ረገድ ቀርነት አለባቸው ቢባልም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የአመራር ሚናቸውን መወጣታቸውን ገልጿል።

እንዲሁም ላይቤሪያ ከ54 ሀገራት በቀረቡት የሞ ኢብራሂም የአፍሪካ መንግስታት ዋና እና ንዑስ መመዘኛዎች መሻሻል ያሳየች ብቸኛ ሀገር ነች።

የቀድሞ ፕሬዚዳንቷ ሁለት የስልጣን ዘመንን በስልጣን ላይ የቆዩ ሲሆን በቅርቡ በተደረገ ምርጫ የቀድሞው የእግር ኳስ ተጫዋቹ ጆርጅ ዊሃ አሸንፎ ስልጣን ይዟል።

ፓርቲያቸውም ለፓርቲ አባል ላልሆነው ተወዳዳሪ ሳይሆን ለጆርጅ ዊሃ ቀስቅሰዋል በማለት ከአባልነታቸው አሰናብቷቸዋል።

ከ2007 ጀምሮ በአግባቡ ሀገራቸውን የመሩ፣ የሕዝባቸውን የኑሮ ደረጃ ያሻሻሉ እና ስልጣን የለቀቁ አፍሪካዊ ፕሬዚዳንቶችን የሚሸልመው ይህ ድርጅት ኤለን ጆንሰን አምስተኛዋ ተሸላሚ ናቸው።

ይህ የ 5ሚሊየን ዶላር ሽልማት ለ 10 ዓመታት የተከፋፈለ ሲሆን በማስከተልም 200000 ዶላር ለእድሜ ዘመን አለው።

ነገር ግን ሁልጊዜም ሽልማቱን የሚወስድ አይኖርም። በስድስት አጋጣሚዎች የትኛውም መሪ ሽልማቱ ይገባዋል ተብሎ ባለመታሰቡ አልተሰጠም።

የቀድሞው የሞዛምቢክ ፕሬዚደንት ዮአኪም ቺሳኖ ለመጀመሪያ ጊዜ የሞ ኢብራሂምን የአምስት ሚልዮን ዶላር ሽልማትን ያገኙ አፍሪካዊ መሪ ናቸው።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement