ችሎት መድፈር ምን ማለት ነው?

                                                

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ የወንጀል ችሎት አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ሶስት ተከሳሾች ላይ ችሎት ደፍራችኋል በማለት ተጨማሪ የስድስት ወር ቅጣት በይኖባቸዋል።

ይህ የመጀመሪያው ሳይሆን በባለፈው ቀጠሮም ችሎትን ደፍራችኋል በሚል የስድስት ወር ቅጣት መጣሉ የሚታወስ ነው። ይህም ጉዳይ ብዙዎች ችሎት መድፈር ምንድን ነው የሚሉ ጥያቄዎችን እንዲያነሱ አድርጓቸዋል።

ችሎት መድፈር በኢትዮጵያ ወንጀል መቅጫ ሕግ አንቀፅ 449 ስር ተደንግጓል።

በዚህም አንቀፅ መሰረት “ችሎትን መድፈር ማለት የችሎቱን ሂደትና ፍርድ አሰጣጥ ላይ ተፅእኖ ማድረስ ነው ” በማለት የህግ ባለሙያ የሆኑትንና በኢትዮጵያ የፍትህ ስርዓት ውስጥ ለብዙ ዓመታት የሰሩት ዶክተር ሄኖክ ገቢሳ ይናገራሉ።

ተከሳሾችና ፍርድ ቤቱን የሚከታተሉ ታዳሚዎች በድምፅ ወይም በማንኛውም እንቅስቃሴ የፍርድ ሂደቱን ካወኩና ፍርድ ቤቱ ስራውን በአግባቡ መቀጠል ካልቻለ ፍርድ ቤቱ እንደተደፈረ እንደሚቆጠር ዶክተር ሄኖክ ይገልፃሉ።

“ይሁን እንጂ አንድ ተከሳሽ መቆም ወይም አለመቆም፤ ተከሳሽ ስሙም በሚጠራበት ወቅት በድምፅ አቤት አለማለት መብት አለው። አንድ ተጠርጣሪ ከዳኛ ጋር መነጋገር ካልፈለገ እስከ ፍርድ ሂደቱ መጨረሻ ያለመነጋገር መብት አለው” ይላሉ ዶክተር ሄኖክ።

የህግ ባለሙያው ጨምረው እንደሚገልፁት በባለፈው ችሎት ደፍራችኋል ተብለው ቅጣት የተጣለባቸውን እነ በቀለ ገርባን በማስታወስ

“እነዚህ ተከሳሾች የተከላካይ ምስክሮች እንዲቀርቡላችው በተደጋጋሚ ለፍርድ ቤቱ ቢያመለክቱም ፍርድ ቤቱ ምላሽ አልሰጣቸውም። በዚህም የተነሳ ሰሚ ስላጡ ችሎቱን በድምፃቸው ብሶታቸውን አሰምተዋል” በማለት ባለሙያው ተናግረዋል።

ሰኞ ዕለት በዋለው ችሎትም ዳኞች ሲገቡ ፖሊስ እስካላዘዘ ድረስ ከመቀመጫቸው መነሳት የግድ አለመሆኑን የሚገልፁት ዶክተር ሄኖክ በሀገራችን የተለመደው አሰራር ግን መቆም ዳኞችን ከመፍራት የተነሳ እንደሆነም ይናገራሉ።

በችሎት ፊት ተነስቶ አለመቆም ችሎትን በመድፈር እንደማያስከስስም ባለሙያው ተናግረዋል።

                                      

የችሎቱን ሂደት በአካል ተገኝቶ ሲከታተል የነበረው ጋዜጠኛው ጌታቸው ሺፈራው የታዘበውን ሲናገር ፍርድ ቤቱ ተከሳሾችን በሚጠራበት ወቅት ሳይነሱ ባሉበት ሆነው እጃቸውን እንዳወጡ ይናገራል።

“የማትቆሙ ከሆነ በፍርድ ቤቱ ደንብ መሰረት እንቀጣችኋለን ብለው ዳኞቹ ቢናገሩም ተከሳሾቹ በእምቢተኝነታቸው ቀጥለዋል። በወቅቱም ከሶስቱ ዳኞች አንደኛው የተከሳሾቹን ማንነት ለመለየት ብቻ እንጂ መቆም አስፈላጊ ላይሆን ይችላል በማለት ለማባበል ሞክረው ነበር። “ይላል።

ተከሳሾቹ በበኩላቸው ባለፈው ችሎት ቆመን እንዳንናገር ስለተከለከልን ዝም እንድንል ስለተገደድን ዛሬ መናገር እንደማይፈልጉ በጠበቃቸው በኩልም መልእክታቸውን እንዳስተላለፉም ጌታቸው ማየቱን ተናግሯል።

ፍርድ ቤቱ ግን ችሎቱን ደፍራችኋል እንዲሁም ከባለፈው ቅጣትም አልተማራችሁም በማለት ሌላ የስድስት ወር ቅጣት ጥሎባቸዋል።

በሌላ በኩል እንዲቀጡ ያደረገው ፍርድ ቤቱን ለ30 ደቂቃ በማስተጓጎል ጊዜ አባክነዋል በሚል ምክንያት ሲሆን ዳኞቹ ራሳቸው ግን ችሎቱ መከፈት ከሚገባው ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ ዘግይተው እንደደረሱ ጌታቸው ይናገራል።

አቃቤ ህግ መንግሥትን በመወከል ተከሳሾችን ለፍርድ ሲያቀርብ ዳኞች ግን ሳይወግኑ ለሁሉም ፍርድ መስጠት ስለሆነ ለተከሳሾች ከለላ መሆን ነበረባቸው የሚለው ዶክተር ሄኖክ ይህ አሰራር ግን በኛ አገር የተለመደ አይደለም ብለዋል።

“እንደኔ ሀሳብ የእነ አቶ በቀለ ገርባ ጉዳይ የግል ጉዳይ አይደለም የህዝብ ነው። በነሱ ላይ የቀረበ ክስም ከፖለቲካ ጋር በመገናኘቱ ይህ ችሎቱን በመድፈር የተወሰነው ውሳኔም ከጀርባው ፖለቲካዊ አላማ አለው። ” ብለዋል ዶክተር ሄኖክ

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement