የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ከሥልጣን እንዲለቁ ግፊት እየበዛባቸው ነው – Pressure Grows On South Africa President To Stand Down

                                                    

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ከገዢው ፓርቲ ኤ ኤን ሲ ከፍተኛ አባላት ጋር ባለፈው እሑድ ከተነጋገሩ በኋላ ከስልጣን እንዲለቁ ከፍተኛ ጫና በዝቶባቸዋል።

በውይይቱ ላይ የተነሱ ጉዳዮች ይፋ ባይደረጉም የፓርቲው አመራሮች አስቸኳይ ስብሰባ ዛሬ ያደርጋሉ ተብሏል።

በተለያዩ የሙስና ወንጀሎች የተከሰሱት ጃኮብ ዙማ ባለፈው ታህሳስ ከኤ ኤን ሲ ፓርቲ መሪነታቸው እንዲለቁ ተደርጎ በሲይሪል ራማፎሳ ተተክተዋል።

እንደተንታኞች ከሆነ በፓርቲው ውስጥ ያለው የሃይል ፍጥጫ በመጪው ዓመት ከሚደረገው ምርጫ ቀደም ብሎ ፓርቲውን ለሁለት ከመክፈሉ በፊት እንዲፈታ የፓርቲው አባላት ይፈልጋሉ።

በዚህም ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማን በህጋዊ መንገድ ወይንም በፓርላማው በኩል ከስልጣን ለማውረድ ጥረት ሊጀምሩ ይችላሉ ተብሏል።

                                                             

ስድስቱ የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ፕሪቶሪያ በሚገኘው የፕሬዝዳንቱ መኖሪያ የደረሱት ለየብቻ ነው ።

ከውይይቱ በኋላ ስለነበራቸው ቆይታ ምንም ያልተናገሩት አመራሮቹ፤ የፓርቲው የሠራተኞች ኮሚቴ ሰኞ እንዲሰበሰብ ጥሪ አቅርበዋል።

የቀድሞ የኤ ኤን ሲ አባል የነበሩት እና አሁን የተቃዋሚ መሪ የሆኑት ጁሊየስ ማሌማ፤ ዙማ ከስልጣን አልለቅም ብለዋል ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

ዙማ እስከ 2019 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ድረስ በበስልጣን መቆየት ይችላሉ።

በፕሬዝዳንቱ ሁለተኛ ዙር የአመራር ወቅት በኢኮኖሚ መቀዛቀዝ እና በሙስና ክሶች ምክንያት የኤ ኤን ሲ ተቀባይነት እየቀነሰ መጥቷል።

ፕሬዝዳንቱ የተለያዩ የሙስና ክሶች ቢቀርቡባቸውም ምንም ጥፋት እንዳልፈጸሙ ተናግረዋል።

በ2019 ፕሬዝዳንት ሆነው ይመረጣሉ በሚል ቅድመ ግምት የተሰጣቸው አዲሱ የኤ ኤን ሲ መሪ ራማፎሳ የፓርቲው አንድነት እንዲጠናከር ጥሪ አቅርበዋል።

ሆኖም ዙማ ከስልጣን የማይለቁ ከሆነ ራማፎሳ እና ደጋፊዎቻቸው ከፕሬዝዳንቱ በተቃራኒ ሊቆሙ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement