የሰሜን ኮሪያ ከፍተኛ ባለስልጣን ደቡብ ኮሪያን ሊጎበኙ ነው – North Korea’s Highest Authority Is To Visit South Korea

                                                             

የክረምት ኦሎምፒክን ተከትሎ በሁለቱ ኮሪያዎች መካከል ያለው ግንኙነት የተሻሻለ በመሰለበት በአሁኑ ወቅት ሰሜን ኮሪያ ከዓመታት በኋላ ከፍተኛ ባለስልጣኗን ወደ ደቡብ ኮሪያ ልትልክ ነው።

በኪም ዮንግ-ናም የሚመራ እና 22 አባላት ያሉት የልዑካን ቡድን በመጪው አርብ ወደ ደቡብ ኮሪያ እንደሚያቀና የደቡብ ውህደት ሚንስትር አስታውቋል።

የሁለቱ ኮሪያ ተወዳዳሪዎች በክረምት ኦሎምፒኩ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ በአንድ ሰንደቅ ዓላማ ስር ይወከላሉ ተብሏል።

ሰሜን ኮሪያ በውድድሩ ላይ መሳተፏ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ለማጠናከር እንደሆነ በፒዮንግያንግ በስፋት ታምኖበታል።

ሰሜን ኮሪያ በኒውክለር እና ሚሳኤል ፕሮግራሞቿ ምክንያት ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ጫና እና ማዕቀብ እየጠነከረባት ይገኛል።

የሃገሪቱ የሙዚቃ ቡድን አባላቷን በመርከብ ወደ ደቡብ ኮሪያ ለመላክ ዕቅድ እንዳላት ባላፈው ሰኞ አስታውቃ ነበር። ይህ ደግሞ በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለው የመርከብ ጉዞ እገዳ መነሳትን የሚፈልግ ነው።

                                           

አጭር የምስል መግለጫአዲስ የተቋቋመው የኮሪያ የበረዶ ሆኪ ቡድን በወዳጅነት ጨዋታ በስዊዲን ተሸንፏል

እንደ የደቡብ የውህደት ሚኒስትር ከሆነ ፒዮንግያንግ የምትፈልገው ማንግዮንግቦንግ 92 የሚባለውን እና በሰሜን ኮሪያ እና ሩሲያ መካከል የሚሰራውን መርከብ ለመጠቀም ነው።

እ.አ.አ ከ2010 ጀምሮ የሰሜን ኮሪያ መርከቦች ደቡብ ኮሪያ ወደብ እንዳይገቡ እገዳ ተጥሎባቸዋል።

ሆኖም በተጀመረው መልካም ግንኙነት መካከል አንዳንድ ችግሮችም አልተፉም።

የክረምት ኦሎምፒኩ ከመጀመሩ ከቀናት በፊት ሰሜን ኮሪያ ትልቅ የጦር ትዕይንት ለማካሄድ አቅዳለች።

ብዙዎች ይህንን ቢተቹትም፤ ሰሜን ኮሪያ ማንም ከዕቅዴ አያጓትተኝም ከማለት በተጨማሪ ከደቡብ ኮሪያ ጋር ልታዘጋጅ የነበረውን ባህል ዝግጅት ሰርዛለች።

ሰሜን ኮሪያን ሁሌም የሚያስቆጣት ሲኦል እና ዋሽንግተን የሁለትዮሽ ወታደራዊ ልምምድ እንዲዘገይ ቢስማሙም ከፓራሎምፒክ ውድድር መጠናቀቅ በኋላ ይካሄዳል ብለዋል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement