ህገወጡ የአረብ አገራት ጉዞ በአዲሱ አዋጅ ይገታል? – Will Illegal Human Trafficking To Arab Countries Be Banned To New Proclamation?

                                                            

በቤት ሰራተኝነት ወደ ተለያዩ አረብ አገራት የሚሄዱ ኢትዮጵያዊያን ላይ የሚደርሰው የአካል ጉዳት፣ስቃይና እንግልት ለዓመታት የማህበረሰብ ራስ ምታት ነበር።

በአሰሪዎች መደብደብ፣ መደፈር፣የጉልበት ብዝበዛ ፣ክፍያ መከልከልና ሌሎችም አስከፊ ስቃዮች ወደ አረብ አገራት የሄዱ በርካታ ኢትዮጵያዊያን እጣ ነበር።

የኢትዮጵያዊያኑን ስቃይ የሚያሳዮ ቪዲዮዎች በማህበራዊ ድረ ገፅ ሲለቀቁ ደግሞ የህብረተሰቡ ቁጣና ቁጭት ያይል ነበር።

ከአራት ዓመት በፊት ሳውዲ ህገወጥ ያለቻቸውን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን ማስወጣትዋን ተከትሎ መንግስት ወደ ተለያዩ አረብ አገራት በቤት ሰራተኝነት የሚደረጉ ጉዞዎችን አገደ።

ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ደግሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዲሱን የኢትዮጵያ የውጭ አገር ሥራ ስምሪት አዋጅ 923/2008 አፀደቀ።

አዋጁ ዜጐች ደህንነታቸውና መብታቸው ተጠብቆና ተረጋግጦ በውጭ አገር በሥራ እንዲሰማሩ የሚያስችሉ ሁኔታዎች መመቻቸትን በሚመለከት ዝርዝር ሁኔታዎችን ያስቀምጣል፡፡

አዋጁ ምን ይላል?

አዋጁ ማን መሄድ ይችላል? ምን ዓይነት ሥልጠናና መሥፈርቶችን አሟልቶ? የኤጀንሲዎችና የአሠሪዎች ግዴታና ኃላፊነትስ ምን ድረስ ነው? የሚሉ ጉዳዮችን ይዘረዝራል፡፡

አዋጁ ከሚያስቀምጣቸው አንኳር ጉዳዮች መካከል ኤጀንሲዎች ወደ ሥራ ለመግባት በግል ከሆነ የአንድ ሚሊዮን ብር፣ በቡድን ከሆነ ደግሞ አምስት ሚሊዮን ብር ካፒታል እንዲኖራቸው በተጨማሪም መቶ ሺሕ ዶላርም ተቀማጭ እንዲያደርጉ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

በተጨማሪም መድህን እንደሚቋቋምና ኤጀንሲዎችም በሚልኩት ሰው ብዛት መሠረት ለመድህኑ እንዲያዋጡ የሚለውም ሌላው ጉዳይ ነው፡፡

አዋጁ ኤጀንሲዎች ላይ የሚያስቀምጠው የገንዘብ መስፈርት ከባድ መሆን ብዙዎቹን ከጨዋታ ውጭ ያደርጋቸዋል የሚል ስጋት ያላቸው አሉ።

በሌላ በኩል አዋጁ ለሥራ ወደ ውጭ አገር የሚሄድ ማንኛውም ሠራተኛ ቢያንስ የስምንተኛ ክፍል ትምህርት ያጠናቀቀና በብቃት ማረጋገጫ የተመሰከረ የሙያ ስልጠና መውሰድ እንዳለበት ያስቀምጣል። አሰሪዎች የሚያስቀምጡትን መስፈርት ማሟላት እነደሚገባም አዋጁ ያስቀምጣል።

ወደ አረብ አገራት በብዛት የሚሄዱት ከገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍል የሚመጡና ከሶስት ከአራተኛ ክፍል በላይ ያልገፉ ከመሆናቸው አንፃር መስፈርቱ የመሄድ ፍላጎት ያላቸውን በርካቶች ይገድባል የሚል እምነት ያላቸው አሉ።

እገዳው ምን ለውጥ አመጣ?

ነገር ግን እገዳው ተጥሎ በነበረባቸው ባለፉት አራት ዓመታት በህገወጥ መንገድ ብዙዎች ወደ ተለያዩ አረብ አገራት ይሄዱ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።

ጉዞው በሱዳንና በኬንያ በኩል በደላሎች እርዳታ ሲደረግ እንደነበርም፤ በቱሪስት ቪዛ ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስተው በሚሄዱባቸው አገራት በሕገወጥ ደላሎችና ኤጀንሲዎች ሥራና የሥራ ፈቃድ አግኝቶ ለመቅረት የሞከሩም በርካታ እንደሆኑ ይነገራል።

በአንድ ወቅት በዚህ መንገድ በዱባይ አየር መንገድ በአንድ በረራ ዱባይ ሄደው ለመቅረት የሞከሩ 30 ኢትዮጵያውያን በአየር መንገዱ ኢሚግሬሽን ተይዘው ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸው ለዚህ አንድ ማሳያ ነው።

ባለፈው ሳምንት ማብቂያም አንድ የቢቢሲ ጋዜጠኛ በተጠቀሰው መንገድ ወደ ዱባይ ሄደው ሳይሳካላቸው በኬንያ አየር መንገድ ወደ ኢትዮጵያ እየተመለሱ የነበሩ ከአስር በላይ የሚሆኑ ሴቶችን አግኝቶ ነበር።

ወ/ሮ ጥሩ ብርሃን ጌትነት በቤት ሰራተኝነት እንጀራ ለማግኘት ወደ ተለያዩ አራብ ሃገራት ሄደው ነገሮች እንዳሰቡት ሳይሆን አእምሯዊና አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸው የሚመለሱ ኢትዮጵያዊያትን የሚያስጠልለውና የሚረዳው ጉድ ሳማሪታን ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ናቸው።

መንግስት እግዱን ጥሎ እያለም ብዙዎች በህገወጥ በመንገድ ወደ አረብ አገራት ይሄዱ እንደነበር ይናገራሉ።

ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት እንኳን ጉድ ሳማሪታን በህገወጥ መንገድ ሄደው ጉዳት ደርሶባቸው የተመለሱ ከ120 በላይ የሚሆኑ ከአረብ አገር ተመላሾችን እንዳስተናገደ ገልፀዋል።

“መንግስት እገዳ ቢጥልም የቆመ ነገር የለም።ምናልባት የደላላ ቁጥር ቀንሶ ሊሆን ይችላል እነጂ።”የሚሉት ወ/ሮ ጥሩ ብርሃን ተጎድተው የሚመለሱት ሴቶች በደላላ በሱዳን፣ጅቡቲና የመን ወደ ተለያዩ አረብ አገራት ሄደው የነበሩ እንደሆኑ ያስረዳሉ።

እሳቸው እንዳሉት በደላላ በቀጥታ በአውሮፕላንም የሚሄዱ አሉ። መንግስት ቢዘጋውም ጉዞው በብዙ መልኩ ሲደረግ የቆየ ሲሆን በሁሉም ሂደት ውስጥ የደላሎች ተሳትፎ አለ።

ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ጉድ ሳማሪታን የሚሄዱት ብዙዎቹ ከቤሩት የሚመለሱ ናቸው።በርካቶቹም በሄዱ ሶስት ወር በማይበልጥ ጊዜ የሚመለሱ እነደሆኑ ከወ/ሮ ጥሩብርሃን ንግግር መረዳት ይቻላል።                              

                                               

 

የኢትዮጵያ የውጭ አገር ሥራ ስምሪት አገልግሎት ሰጪ ኤጀንሲዎች አሠሪ ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ መዝገቡ አሰፋ ኤጀንሲዎቹ ላይ ወደ 12 የሚሆኑ መስፈርቶች መቀመጣቸውን ይጠቅሳሉ።

አንዳንዶቹ መስፈርቶች ስነምግባር በጎደለው መንገድ የሚሰሩና እንዲሁ ያለዝግጅት ወደ ስራው ዘው ብለው የሚገቡ ኤጀንሲዎችን ለመገደብ ታስበው የወጡ ቢሆንም ከባድና ተፈፃሚነታቸው እንደሚያስቸግር ይናገራሉ አቶ መዝገቡ።

እሳቸው እንደሚሉት መቶ ሺህ ዶላር ማስያዝ ለብዙዎቹ ኤጀንሲዎች ከባድ ነው።

በሌላ በኩል የዜጎች መብት የሚጣሰው የት ጋር ነው የሚለውን በደንብ መመልከት ያስፈልጋል።

አዋጁ ላይ ስለተቀመጡ ብቻም ሳይሆን በተቀባይ አገር ላይ ያሉ በተግባር መታየት ያለባቸው ነገሮችም አሉ።

“ችግር ቢያጋጥማቸው በተቀባይ አገር ማን ይደርስላቸዋል?ከኤምባሲ ጋር ያላቸው ግንኙነትስ ምን መሆን አለበት?የሚሉና መሰል ጉዳዮች ተግባራዊነት በጥንቃቄ ሊታይ ይገባል። ነገሩ በኤጀንሲዎች ላይ ብቻ የሚጣል አይደለም።”ይላሉ።

ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ግን የገንዘብ መስፈርቱ ችግር እንዳልሆና እስካሁን 980 ኤጀንሲዎች ፎርም እንደወሰዱና ማመልከቻ እንዳስገቡ አስታውቋል።

የሚኒስቴር መስሪያቤቱ የውጭ አገር ስራ ስምሪት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አበራ መስፈርቱን አሟልተው የተገኙ 20 ኤጀንሲዎች የብቃት ማረጋገጫ እንዳገኙ ተናግራዋል።

እስካሁን ከ980 ፍቃድ ያገኙት 20 ብቻ መሆን በራሱ ግን የሚናገረው ነገር ለመኖሩ አያጠራጥርም።

የአገሪቱን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነትን ታሳቢ በማድረግ የተጓዦችን የትምህርት ደረጃ የሚመለከተው መስፈርትም ችግር እንደማይሆን አቶ ብርሃኑ ይናገራሉ።

ነገር ግን ባለፉት አመታት በገፍ ወደ አረብ አገራት ሲሄዱ የነበሩት ማንበብ እነኳ የማይችሉ የመሆናቸው እውነታ ደግሞ የሚናገረው ተቃራኒውን ነው።

እገዳው ተጥሎ ህገወጡ ጉዞ እንደቀጠለ ነበር።

ኤጀንሲዎችና ተጓዦች አዲሱ የስራ ስምሪት አዋጅ የሚጠይቃቸውን መስፈርቶች ማሟላት ካልቻሉ ህገወጡ ጉዞ ተጠናክሮ ይቀጥላል የሚለው ስጋት የብዙዎች ነው።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement