NEWS: አሜሪካ የሃማስን መሪ በሽብርተኝነት መዝገብ አሰፈረች – US Designates Hamas Leader As Terrorist

                                                

የአሜሪካ መንግሥት የፍልስጤሙን ቡድን ሃማስ መሪ በሽብርተኝነት መዝገብ ውስጥ አስፍሮ እገዳ ጥለ።

እንደሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ከሆነ ኢስማኤል ሃኒያ “ከሃማስ ወታደራዊ ክንፍ ጋር ካለው ቅርብ ግንኙነት” በተጨማሪ “የትጥቅ ትግልን ያበረታታል።”

አሜሪካ፣ እስራኤል፣ የአውሮፓ ህብረት እና እንግሊዝ ሃማስን ከዚህ ቀደም በሽብርተኝነት መፈረጃቸው ይታወሳል።

የሃኒያን በሽብርተኛነት መዝገብ መስፈር “ጥቅም የሌለው ነው” ሲል ሃማስ ውሳኔውን ነቅፏል።

ውሳኔው “እስራኤልን በፍጥነት ከያዘቻችው አካባቢዎች የማስወጣቱን እና የመከላከሉን ሥራ አያስተጓጉለውም” ብሏል ቡድኑ በመግለጫው።

እ.አ.አ ከ2008 በኋላ ሃማስ ከእስራኤል ጋር ሦስት ጊዜ ጦርነት ውስጥ የገባ ሲሆን ጥቃት አድርሶ 17 አሜሪካዊያንን በመግደልም በአሜሪካ ተጠያቂ ተደርጓል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሦስት የታጣቂ ቡድኖችንም በሽብርተኝነት ጥቁር መዝገብ ላይ አስፍሯል።

በኢራን የሚደገፈው እና በጋዛ እና በዌስት ባንክ የሚንቀሳቀሰው ሃራካት አል-ሳብሪን፣ በግብፅ ቃለዩቢያ እና ሜኑፊያ የሚንቀሳቀሰው ሊዋ አል-ታውራ እና ሌላኛው የግብፅ ቡድን ሃስም ናቸው በሽብርተኛነት ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት።

“ይህ ውሳኔ ዒላማ ያደረገው ለመካከለኛውን ምሥራቅ መረጋጋት ስጋት የሆኑ፣ የሠላም ድርድሩን የማይቀበሉትንና ወዳጆቻችን የሆኑትን ግብፅ እና እስራኤልን የሚያጠቁትን ቁልፍ የሽብር ቡድኖችን እና መሪዎቻቸውን ነው” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሬክስ ቲለርሰን አስታውቀዋል።

“ውሳኔው የሽብር ድርጊት ለመፈጸም የሚያስችላቸውን ዕቅድ እና ተግባር እንዳይፈጽሙ የሚያደርግ ነው” ብለዋል።

ምንጭ:- ቢቢሲ

Advertisement