NEWS: በየመን ጦርነት ከ5 ሺህ በላይ ህፃናት ሞተዋል- ዩኒሴፍ – UNICEF: Over 5,000 Kids Killed by Saudi War on Yemen

                                                                                  

ሳዑዲ አረቢያ መራሹ ጦር በየመን እያካሄደ ባለው ጦርነት የበርካታ ህፃናት ህይወት እንዲያልፍ ማድረጉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት አድን ኤጀንሲ አስታወቀ።

ዩኒሴፍ ትናንት ባወጣው መረጃ ጦርነቱ ከተጀመረበት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከየካቲት ወር 2015 ጀምሮ እስካሀን ባለው ጊዜ ውስጥ ከ5 ሺህ በላይ ህፃናት ህይወታቸው አልፏል።

ይህ አሃዝም በአማካይ በቀን የ5 ህጻናት ህይወት እንደሚያልፍ ያሳያል ነው ያለው ሪፖርቱ።

እንዲሁም ከ2 ሚሊየን በላይ የመናውያን ህፃናት ከትምህረት ገበታ ውጭ ለመሆን ተገደዋል ያለው ሪፖርቱ፥ ከ400 ሺህ በላይ የሚሆኑት ህፃናት ደግሞ ለምግብ እጥረት መጋለጣቸውን አስቀምጧል።

ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ከ3 ሚሊየን በላይ ህፃናት ተወልደዋል የተባለ ሲሆን፥ እነዚህ ህፃናትም በግጭቶች፣ ከመኖሪያ መፈናቀል፣ በሽታ፣ ድህነት እና የምግብ እጥረት ስጋት ውስጥ የወደቁ መሆናቸውም በሪፖርቱ ተብራርቷል።

በየመን የዩኒሴፍ ተወካይ ሜሪክሴል ሬናሎ፥ “አዲሱ የየመን ትውል ግጭትን ብቻ እያቀ ነው በማደግ ላይ የሚገኘው፤ ሀገሪቱ የሚገኙ ህፃናት በጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው ነው” ብለዋል።

የተባበሩት ምንግስታት ድርጅት ቀደም ብሎ ባወጣው ሪፖርት በእርዳታ ላይ ጥገኛ የሆኑ የመናውያን ቁጥር 22 ነጥብ 2 ሚሊየን ደርሷል።

የየመን ጦርነት እንደ አውሮፓውያኑ 2015 ከተጀመረ ወዲህ እስካሁን ከ13 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸውንም ሪፖርቱ ያመለክታል።

በጦርነቱ ምክንያት በርካታ የመሰረተ ልማቶች በመውደማቸውም በሀገሪቱ የኮሌራ ወረርሽኝ መከሰቱን ደግሞ የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣው ሪፖርት ያመልከታል። 

ድርጅቱ ባወጣው ሪፖርት በወረርሽኙ 2 ሺህ 167 ሰዎች የሞቱ ሲሆን፥ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ሰዎች ደግሞ በበሽታው ተጠቅተዋል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement