የከተራና የጥምቀት በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ዝግጅት ተጠናቋል – All Arrangements and Pre-questions are Taken To Celebrate Ethiopian Ketera in Piece

                                                                 

የከተራና የጥምቀት በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ዝግጅት ማጠናቀቁን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ የከተራ እና የጥምቀት በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ከበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴ፣ ከፀጥታና የፍትህ አካላት እንዲሁም ከመዲናዋ ነዋሪ ጋር እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በዓላቱ በሰላም ተጀምረው እንዲጠናቀቁ ለወንጀል እና ትራፊክ አደጋ መከላከል ተግባሩ ልዩ ትኩረት በመስጠት በርካታ የሰው ኃይል ማሰማራቱንም ኮሚሽኑ ገልጿል።

በታቦት ማደሪያ ስፍራዎች በተለይም በርካታ የበዓሉ ታዳሚዎች በሚገኙበት ጃን ሜዳ ግቢ ውስጥ፥ ምርመራ በማጣራት አፋጣኝ ውሳኔ መስጠት የሚያስችል ጊዜያዊ ፖሊስ ጣቢያ አገልግሎት የሚሰጥ ይሆናል። 

ህብረተሰቡ ፀበል በሚረጭበት ወቅት በሚፈጠር ግፊያ ጉዳት እንዳይደርስበት፣ ንብረቶቹ እንዳይሰረቁበት እንዲሁም የመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አለበትም ነው ያለው ኮሚሽኑ።

የእምነቱ ተከታዮች በተለይ ወጣቶች ከዚህ በፊት እንደሚያደርጉት ሁሉ በተደራጀ መንገድ ከፖሊስ እና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጎን በመቆም ለበዓሉ በሰላም መከበር የሚያደርጉትን ትብብር እንዲቀጥሉ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡ 

ታቦታት በሚያልፉበት ወቅትም አሽከርካሪዎች ሆኑ የበዓሉ ታዳሚዎች ለፀጥታ አካላት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉም ኮሚሽኑ ጥሪውን አቅርቧል።

ለዚህም ከጥር 10 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በዓሉ እስከሚጠናቀቅ ድረስ በጃን ሜዳ ዙሪያ ተሽከርካሪ ለአጭርም ሆነ ለረጅም ጊዜ አቁሞ መሄድ የተከለከለ መሆኑን አሽከርካሪዎች ተገንዝበው አማራጭ ስፍራዎችን እንዲጠቀሙ አሳስቧል። 

ህብረተሰቡ በማንኛውም ወቅት ከፀጥታ ስራ ጋር ተያያዥ እና አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት ጥቆማ ለመስጠት እንዲሁም የፖሊስ አገልግሎትን ለማግኘት፥

በ01-11-26-43-77፣ 01-11-26-43-59፣ 01-18-27-41-51፣ 01-11-11-01-11 እና በ991 ወይም 916 ነፃ የስልክ መስመሮችን መጠቀም እንደሚችል ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

 

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

Advertisement