በመዲናዋ በተንቀሳቃሽ ቄራ የእርድ አገልግሎት ሊጀመር ነው – Mobile Slaughtering Service is Going to Start in Addis Abeba

                                                        

በአዲስ አበባ በተንቀሳቃሽ ቄራ የእርድ አገልግሎት ሊጀምር መሆኑን የከተማዋ ቄራዎች ድርጅት አስታወቀ።

በተለይም በበዓላት ወቅት በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ሕገ-ወጥ የእንስሳት እርድ እየተባባሰ በመምጣቱ ንጽህናውን ባልጠበቀ ስጋ እና በአካባቢ ብክለት ምክንያት ነዋሪዎች ለተለያዩ ህመሞች ይጋለጣሉ።

ህብረተሰቡ የሚመገበውን ስጋ ከጤናማ እንስሳት የተገኘ መሆኑን የሚያረጋግጥበት መንገድ ባለመዘርጋቱ፣ የቄራዎች ድርጅት ተደራሽ አለመሆንና በአመለካከት ጉድለት ሳቢያ በህገ ወጥ እርድ የሚገኝ ስጋን ለመመገብ ምክንያቶች ናቸው።

ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፥ በአዲስ አበባ እርድ በብዛት በሚፈጸምባቸውን በዓላት ብቻ ከ20 ሺህ በላይ ከብቶች በሕገ-ወጥ መንገድ ይታረዳሉ።

በሕገ-ወጥ እርድ ምክንያት መንግሥት ማግኘት ከሚገባው ገቢ ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ እንደሚያጣም ተጠቅሷል። 

ይህን የተረዳው የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት በማዕከል ከሚዘጋጅ የስጋ ማዕከል በተጨማሪ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በመዟዟር አገልግሎቱን ሊጀምር መሆኑን አስታውቋል፡፡ 

የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ንብረት በቃ እንደገለጹት፥ ድርጅቱ የእርድ አገልግሎቱን ሕዝቡ በሚፈልገው ደረጃ ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ውስንነቶች ይስተዋላሉ። 

በመሆኑም ተንቀሳቃሽ ቄራው የእርድ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ሕገ ወጥ እርድን ከመከላከል ባለፈ ጤንነቱ የተጠበቀ ሥጋ ለሕብረተሰቡ ማድረስ ያስችላል ብለዋል።

አገልግሎቱን ለመጀመር ድርጅቱ ከሣይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ጥናቶችን እያካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

አገልግሎቱ በርካታ ሕዝብ በሚገኝባቸው በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ላይ የሚከናወን መሆኑ ሕብረተሰቡን ተደራሽና ተጠቃሚ በማድረግ በተለይም በበዓላት ወቅት የሚፈጸሙ ሕገ-ወጥ እርድን ለመከላከል ይረዳል ነው ያሉት።

እንደ አቶ ንብረት ገለጻ ከሆነ፥ የእርድ አገልግሎት የሚሰጠው ተንቀሳቃሽ ቄራው ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የያዘ ሲሆን፤ አስፈላጊ ነገሮችን በማሟላት በሚቀጥለው ዓመት አገልግሎት መስጠቱን ይጀምራል ብለዋል። 

የተንቀሰቃሽ ቄራዎች ቴክኖሎጂ እንደ አሜሪካ፣ ቻይና፣ አውስትራሊያና ካናዳ ባሉ የበለፀጉ ሀገራት በስፋት አገልግሎት እንደሚሰጥ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement