ሁሉንም የምትመለከተው ቻይና፡ የዓለማችን መጠነ ሠፊው የደህንነት ካሜራ አውታረ መረብ – In Your Face: China’s All-seeing State

                                                         

በቻይና በሚገኝ አንድ ከተማ እተጓዙ ነው። በትንሽ እርምጃ ርቀት አንድ፣ ሁለት ወይም ሦስት የደህንነት ካሜራዎች የሚያጋጥሞት ሲሆን በዚህ ወቅት ፖሊስ ስለ እርሶ ሙሉ መረጃ ለማግኘት ይችላል።

ቻይና “የዓለማችንን እጅግ ውስብስብ የደህንነት ካሜራ” እየሰራች ነው። 1.3 ቢሊዮን ህዝቧን ለመከታተልም በአሁኑ ወቅት 170 ሚሊዮን ካሜራዎች በመላ ሃገሪቱ በሥራ ላይ ውለዋል።

በቀጣይ ሦስት ዓመታት ደግሞ 400 ሚሊዮን የደህንነት ካሜራዎች ይገጠማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አብዛኛዎቹ እነዚህ ካሜራዎች እጅግ በረቀቁ ቴክኖሎጂዎች የታገዙ ናቸው። አንዳንዶቹ የሠው ፊት መለየት የሚያስችሉ ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ የአንድን ሠው ዕድሜ፣ ዘር እና ጾታ መለየት ይችላሉ።

ይህ ደግሞ ባለስልጣናት የመንገደኛን ምስል በመውሰድ ካላቸው መረጃ ጋር በማመሳከር ሙሉ መረጃ ከማግኘት በተጨማሪ እንቅስቃሴንም ለመቆጣጠር ይችላሉ።

ዘዴው ተጠርጣሪ ተብሎ የተሰየምን ፊት ሲያገኝ ወደ መቆጣጠሪያ ክፍል የማንቂያ መልዕክት ያስተላልፋል። በዚያውም ለፖሊስ መልዕክቱን ያደርሳል።

ለሙከራ ተብሎ የቢቢሲው ባልደረባ ጆን ሱድዎርዝ በቻይናዋ ጉይያንግ ከተማ ከሚገኙ ካሜራዎች በአንዱ ተለይቶ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ለመዋል የፈጀበት ሰባት ደቂቃ ብቻ ነበር።

“ፊትን ከመኪናው ባለቤት፣ ዘመዶች እና ከሚገናኛቸው ሰዎች ጋር እናያይዛለን” ሲሉ አንድ ሚሊዮን ካሜራዎችን የሸጠው የዳሁአ ቴክኖሎጂ የጥናትና ምርምር ምክትል ፕሬዝዳንት ዪን ጁን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

“ብዙ ካሜራዎችን በመጠቀም በብዛት ማንን እንደሚያገኙም ማወቅ እንችላለን” ሲሉ ይገልጻሉ።

                                                                             

ምንም መደበቅ ምንም መፍራት አያስፈልግም?

እንደባለስልጣናቱ ከሆነ ይህ አስደናቂ የደህንነት ካሜራ ወንጀልን መከላከል ብቻ ሳይሆን ለመገመትም የሚረዳ ነው።

“የግለሰቦችን መረጃ የምንመለከተው እነሱ የእኛን ድጋፍ ሲፈልጉ ብቻ ነው” ሲሉ በጉዪያንግ የፖሊስ ባልደረባ የሆኑት ዡ ያን ይገልጻሉ። “እነሱ ካልፈለጉት ባለን ትልቅ የመረጃ ቋት ውስጥ የሚቀመጥ ሲሆን አስፈላጊ ሲሆን ብቻ አውጥተን የምንጠቀመው ይሆናል” ብለዋል።

ምንም መደበቅ የሌለባቸወ ዜጎች “ስለምንም መፍራት የለባቸውም” ሲሉም ጨምረው ያስረዳሉ።

ይህ ሃሳብ ግን ሁሉንም አያስማማም።

ጂ ፌንግ መንግሥትን በሚተቹት ግጥሞቹ ይታወቃል። ቤጂንግ ውስጥ በአርቲስቶች መኖሪያነት በምትታወቀው አካባቢ ይኖራል። እንደእርሱ ዕምነት ከሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደጥቃት አድራሽ ተቆጥረዋል።

“ሁሌም የሚከታተል እንዳለ ይሰማሃል” ሲል ለቢቢሲ ይገልጻል።

“ምንም ነገር ሥራ ሁሌም የማይታዩ ዓይኖች እየተከታተሉህ ነው።”

እነዚህ በቴክኖሎጂ የረቀቁ የደህንነት ካሜራዎች የፖሊስን ሥራ ቀላል አድርገዋል። “ይህ ነዋሪዎችን የመሰለል ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ይላል ገጣሚው።

እንደሂዩማን ራይትስ ዎች ያሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እንደሚሉት የቻይና መጠነ ሠፊ መረጃ አሰባሰብ “ግላዊ መብትን” የሚጥስ እና “የነዋሪዎችን እንቅስቃሴ መከታተል እና መገመትን” ትኩረቱ ያደረገ ነው።

                                                                        

በጥያቄዎች መካከል የሚደረግ ማስፋፋት

የእነዚህ ካሜራዎች መመረት ብዙ ጥያቄዎችን አስነስቷል።

“ምቾት የማይሰጥ ነገር አለው” ይላሉ የዳሁአ ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር የሆኑት ዳንኤል ቻኡ ለቢቢሲ።

“ቴክኖሎጂው በራሱ ሠዎች እንዲጠቀሙበት የተሰራ ቢሆንም በሽብርተኞች እጅ ከገባም የሚጎዳም ነገር አለው።”

አሁን በትክክል እየሆነ ያለው ነገር በቻይና የደህንነት ካሜራዎች ቁጥር እያደገ መሆኑ ነው።

እንደሮይተርስ ዘገባ ከሆነ ብዙ የቻይና እና የውጭ ኢንቨስተሮች የሠውን ፊት መለየት በሚችል የቴክኖሎጂ ዘርፍ ላይ በስፋት እየተሰማሩ ነው።

አይኤችኤስ እንደተባለው ተቋም ከሆነ እ.አ.አ በ2016 ከደህንነት ካሜራ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በቻይና 6 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጓል።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement