የኢትዮጵያ አየር መንገድና የዛምቢያ መንግስት የ30 ሚሊየን ዶላር ስምምነት ተፈራረሙ – Ethiopian Airlines and Zambia Government Signed a $ 30 Million Deal

                                                              

ኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የዛምቢያ መንግስት የሀገሪቱን ብሄራዊ አየር መንገድ ስራ ለማስጀመር የ30 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱም የሀገሪቱ መንግስት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመሆን የዛምቢያ የአር መንገድን በአውሮፓውያኑ የቀን አቆጣጠር በቀጣይ ጥቅምት ወር 2018 ስራ ለማስጀመር ነው የተደረገው ተብሏል።

የዛምቢያ ትራንስፖርት እና ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስትር ቢራን ሙሺምባ በሰጡት ማብራሪያ፥ የፕሬዚዳንት ኤድጋር ሉንጉ ካቢኔ የዛምቢያ አየር መንገድ ፕሮጀክትን በይፋ አፅድቋል።

እንደ አዲስ ስራ የሚጀምረው የዛምቢያ አየር መንገድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በጥምረት እንደሚሰራ የገለጹት ሚኒስትሩ፥ ለዚህም ይሆን ዘንድ የ30 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በጀት መጽደቁን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም ቀደም ብለው ሰጥተውት በነበረው ማብራሪያ፥ የዛምቢያ አየር መንገድ ዳሽ 8-400 እና ቦይንግ 737 አውሮፕላኖች ስራውን መስራት ሊጀምር እንደሚችል ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ እንደ አዲስ በይፋ ስራ የሚጀምረውን የዛምቢያ አየር መንገድ 45 በመቶ ድርሻ እንደሚይዝ መነገሩ ይታወሳል።

ቀሪውን 55 በመቶ የዛምቢያ አየር መንገድ ድርሻ ደግሞ የሀገሪቱ መንግስት እንደሚይዝ ነው በወቅቱ የተነገረው።

ዛምቢያ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ለመስራት ከስምምነት የደረሰች ሁለተኛዋ ደቡብ አፍሪካዊት ሀገር ነች።

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመስራት ላይ የምትገኘው ሌላኛዋ ደቡብ አፍሪካዊት ሀገር ማላዊ ናት።

የማላዊ የአየር መንገድን ድርሻ የሀገሪቱ መንግስት 51 በመቶውን እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደግሞ 49 በመቶ ይዘው ነው በመስራት ላይ የሚገኙት።

የማላዊ የአየር መንገድ በአሁኑ ወቅት ቦይንግ 737 እና Q400 አውሮፕላኖችን ተጠቅሞ በመስራት ላይ ሲሆን፥ ሞዛምቢክ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዚምባቡዌ እና ኬንያን ጨምሮ ሰባት መዳረሻዎች አሉት።

 

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

Advertisement