ሰሜን ኮሪያ ለመወያየት ፈቃደኛ መሆኗን ገለፀች – North Korea Accepts Olympics Talks Offer

                                                          

ሰሜን ኮሪያ በሚቀጥላው ሳምንት በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ ሊደረግ በታቀደ ውይይት ላይ እንድትሳተፍ የቀረበላትን ግብዣ መቀበሏን የደቡብ ኮሪያ ባለስልታናት ተናገሩ።

በመጪው ማክሰኞ የሚደረገው ውይይት ደቡብ ኮሪያ የካቲት ወር ላይ በምታስተናግደው የክረምት ኦሊምፒክ ላይ የሰሜን ኮሪያ ስፖርተኞች የሚሳተፉበትን መንገድ በመፈለግ ላይ ያተኩራል።

የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በዚህ ሳምንት እንዳሉት ስፖርተኞቻቸውን በውድድሩ እንዲሳተፉ ወደ ደቡብ ኮሪያ መላክ ”አንድነታችንን ለማሳየት ጥሩ አጋጣሚ ነው” ብለው ነበር።

ውይይቱ ፓንሙንጆም በሚባለው ሁለቱን ሃገራት በሚያዋስነው መንደር ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

የሰላም መንደር ተብሎ የሚጠራው ይህ ስፍራ በከፍተኛ ደረጃ ጥበቃ የሚደረግለት ከወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ነፃ የሆነ ቦታ ሲሆን ሁለቱ ሃገራት የሰላም ንግግር የሚያደርጉበት ታሪካዊ መንደር ነው።

በደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት ያሉ አንድ ባለስልጣን እንደተናገሩት፤ የውይይቱ ቀዳሚ ጉዳይ የፒዮንግቻንግ የክረምት ኦሊምፒክ ነው።

ይሁን እንጂ ባለስልጣኑ ዮንሃፕ ለተባለው የደቡብ ኮሪያ ዜና ወኪል እንደተናገሩት ”ሰሜን ኮሪያ የክረምት ኦሊምፒክ ተሳትፎዋን ካጠናቀቀች በኋላ የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት ለማሻሻል ውይይት ይደረጋል” ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ እነማን እንደሚሳተፉ እስካሁን ግልፅ ባይሆንም፤ ከሁለት ዓመት ወዲህ የተካሄደ ከፍተኛ ባለስልጣናት የሚሳተፉበት የመጀመሪያው ውይይት ይሆናል።

የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ሙን ጃኢ-ኢን ቀደም ሲል እንደተናገሩት የክረምቱ ኦሊምፒክ በፍጥጫ ላይ ያሉት ሁለቱ ሃገራት ግንኙነታቸውን ለማሻሻል ”መልካም አጋጣሚ” ነው ብለው ነበር።

በዚህ ሳምንት መግቢያ ላይም የመጀመሪያውን ግንኙነት ያስጀመረው በድንበር አካባቢ የአስቸኳይ የስልክ ግንኙነት መስመርን መልሳ በመክፈት ለሂደቱ ጅማሬ ሰሜን ኮሪያ ፈቃደኝነቷን አሳይታለች።

ነገር ግን የደቡብ ኮሪያ የውህደት ሚኒስቴር ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል እንደገለፀው ሰሜን ኮሪያ ለቀረበላት የውይይት ግብዣ ምላሽ የሰጠችው ዛሬ አርብ በተላከ የፋክስ መልዕክት ነው።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement