NEWS: አሜሪካ ‘ዋናክራይ’ ለተሰኘው የሳይበር ጥቃት ሰሜን ኮሪያን ጥፋተኛ አደረገች – White House Blames North Korea For WannaCry Cyber Attack

                               

የዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር ‘ዋናክራይ’ ለተሰኘውና ሆስፒታሎችን፣ የንግድ ተቋማትና ባንኮች ላይ ጉዳት ላደረሰው ዓለም አቀፍ የበይነ-መረብ ጥቃት ሰሜን ኮሪያ ቀጥተኛ ተጠያቂ እንደሆነች አስታወቀ።

በ150 ሃገራት የሚገኙ 300ሺህ ኮምፒዩተሮች ላይ ጥቃት ያደረሰው ይህ ቫይረስ በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ጉዳት አድርሷል።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ ረዳት ቶማስ ቦሰርት ‘ዎል ስትሪት’ በተሰኘው ጋዜጣ ላይ ነው ይህንን ክስ ያቀረቡት።

ይህም ዩናይትድ ስቴትስ ሰሜን ኮሪያን ለቫይረሱ ጥቃት በይፋ ጥፋተኛ ስታደርግ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። የፕሬዚዳንቱ በሃገር ደህንነት ጉዳዮች የሚያማክሩት ቶማስ ክሱ በመረጃ የተደገፈ መሆኑን አሳውቀዋል።

የእንግሊዝ መንግሥትም ጥቃቱ በሰሜን ኮሪያ መፈፀሙን በእርግጠኝነት ባለፈው ወር ይፋ አድርጎ ነበር።

ባለፈው ግንቦት የዊንዶውዝ ኮምፒውተርስ ተጠቃሚዎች በሳይበር ጥቃቱ ምክንያት መረጃዎቻቸውን ማግኘት ባለመቻላቸው ለማስመለስ እንዲከፍሉ ተጠይቀው ነበር። ዩሮፖል የተሰኘው የአውሮፓ ሕብረት የፖሊስ አካል የጥቃቱ ክብደት ‘ታይቶ የማይታወቅ’ በማለት ጠቅሶታል።

                                                      

ለጋዜጣው በሰጡት መግለጫ ቶማስ ሰሜን ኮሪያ ለጥቃቱ ተጠያቂ መደረግ እንዳለባትና ዩናይትድ ስቴትስ ‘ከባድ ጫና’ በመጠቀም የሳይበር ጥቃቶችን ለመፈፀም ያላትን ፍላጎት እንደምታከሽፍ ተናገረዋል።

ግኝታቸውን አስከትሎ ግን ዩናይትድ ስቴትስ ምን ዓይነት እርምጃዎችን ለመውሰድ ዝግጁ እንደሆነች አላብራሩም።

ባለፈው ወር ‘የሽብር ድርጊት ተባባሪ መንግሥት’ የሚለው ስያሜ በድጋሚ ሲሰጣት ከባድ የኢኮኖሚያዊ እገዳዎች የተጣለባት ሰሜን ኮሪያ፤ እያካሄደች ባለው የኒዩክሌር ሚሳይል ሙከራዎች ምክንያት ውጥረት ተፈጥሯል።

”ሰሜን ኮሪያ ከአስርታት በላይ በተለየ መልኩ ያልተገሩ መጥፎ እርምጃዎችን ወስዳለች፤ እያሳየች ያለው ተንኮል አዘል አካሄድም ዕለት ተለት ከመጠን እያለፈ ነው። ‘ዋናክራይ’ ሁሉንም የሚያጠቃ ቫይረስ ነበር” በማለት ቶማስ ተናግረዋል።

በመቀጠልም ”በይነ-መረብን (ኢንተርኔት) ከጥቃት ነፃ ለማድረግ እየጣርን ባለንበት ሰዓት፤ ብቻቸውን ሆነ ከሕገ-ወጥ ድርጅት ጋር በመተባበር ወይም ከጠላት ሃገራት ጋር በማበር ጥቃት የሚያደርሱብንንና የሚያስፈራሩንን ተጠያቂ ከማድረግ ወደኋላ አንልም” ብለዋል።

በተጨማሪም ”የአምባገነኖች ማሣሪያ አደገኛ ከመሆናቸው የተነሳ ችላ ማለት አይቻለም” ሲሉ ገልጸዋል።

በዕለተ ማክሰኞም ከዋይት ሃውስ ፒዮንግያንግን ተጠያቂ የሚያድረግ መግለጫ ይጠበቃል።

‘ታይቶ የማይታወቅ ጥቃት’

የእንግሊዝ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት (ኤንኤችኤስ) በዚህ ሳይበር ጥቃት በይበልጥ ከመጎዳቱ የተነሳ ብዙ ታካሚዎችን ከቀጠሮና ከቀዶ ሕክምና መመለስ ነበረባቸው።

ጥቃቱ በዓለም ዙሪያ ተዳርሶ የሩሲያም የፖስታ አገልግሎት ከጥቃቱ ጉዳት አልተረፈም።

                                                

እ.አ.አ በ2014 የሶኒ የፊልም አምራች ኪም ጁንግ ኡን የሚገደልበት በልብ ወለድ ላይ የተመሠረተ ፊልም እንደለቀቀ የሳይበር ጥቃት በደረሰበት ጊዜ ዩናይትድ ስቴትስ የሰሜን ኮሪያ ሸር እንደሆነ ተናግራ ነበር።

የመዝናኛው ድርጅቱ ፊልም፣ ገንዘብ ነክ መረጃዎችና የግል ኢሜይሎች በበይነ-መረብ ይፋ ሆነው ነበር።

በክሱ ዙሪያ ሰሜን ኮሪያ ለፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ምላሽ ቢሰጡም በዋይት ሃውስ ስለ ‘ዋናክራይ’ ጥቃት ለቀረበው ክስ ግን መልስ አልሰጡም።

ባለፈው ጥቅምት ሰሜን ኮሪያ ከእንግሊዝ መንግሥት የቀረባበትን ክስ ‘መሠረት የሌለው ግምትና’ ዓለም አቀፋዊ እገዳዎችን ለማጠናከር የታሰበ ‘የክፋት ሙከራ’ ነው ብለው ነበር።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement