የግሉ ዘርፍ ሠራተኞች ለመውለድ ምን ያህል ይጠብቁ? – Private Company Female Employees and Pregnancy

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ረቡዕ ህዳር 26 ቀን 2010 ዓ.ም ባካሄደው የሶስተኛ ዓመት 7ኛ መደበኛ ስብሰባ የተሻሻለውን የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ በማፅደቅ የመንግሥት ሰራተኞችን የወሊድ ፈቃድ ከሦስት ወደ አራት ወር ከፍ እንዲል አድርጓል።

አዋጁ በብዙዎች እሰይ የተባለለት ቢሆንም የአዋጁን መፅደቅ ተከትሎ በግሉ ዘርፍ ያሉ እናቶችስ? የሚል ጥያቄ እየተነሳ ነው።

አንድ አገር ላይ እየሰሩና እኩል ግብር እየከፈሉ እንዴት የዚህ ዓይነት ልዩነት ይኖራል በሚል አስተያየታቸውን የሰነዘሩ ብዙዎች ናቸው።

በግሉ ዘርፍ ያሉ ሴቶችን ጉዳይ በተመለከተ ከቢቢሲ ጥያቄ የቀረበላቸው የፌደራል የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር ህግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተክይበሉ በግሉ ዘርፍና በመንግሥት በጀት በማይተዳደሩ የልማት ድርጅቶች የአሰሪና ሠራተኛ ግንኙነትን የሚመለከት ሌላ አዋጅ መኖሩን በማስታወስ ይህ አዋጅም ተሻሽሎ ተመሳሳይ ውጤት እንደሚኖር ገልፀዋል።

“የአሰሪና ሠራተኛ አዋጁ በመሻሻል ላይ ነው። በመሰረታዊነት የሚታየው ወሊድ ሴት ልጅ ትውልድን የመተካት ሃላፊነት የምትወጣበት ተፈጥሯዊ ነገር መሆኑ ነው። ስለዚህ ተመሳሳይ የሆነ የፖሊሲ አቋም ይኖራል ተብሎ ነው የሚጠበቀው። እስከዛሬም የነበረው ነገር ተመሳሳይ ነው” ብለዋል አቶ ደረጀ።

ነገር ግን ይህ በግሉ ዘርፍ ያሉ ሴቶች የወሊድ ፈቃድን የሚመለከተው አዋጅን የማሻሻል ሂደት ገና በጅምር ላይ ነው።

አቶ ደረጀ እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ማሻሻያውን እያየውና እየመከረበት ሲሆን ለውሳኔ አልደረሰም።

እዚህ ጋር ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ ለግል ዘርፍ ሠራተኞች የተዘጋነው አዋጅ በትክክል መቼ ይፀድቃል የሚለው ነው።

ለመንግሥት ሠራተኞች የፀደቀው አዋጅ በተጨማሪም የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የህፃናት ማቆያ እንዲያዘጋጁም ይደነግጋል።

ያነጋገርናቸው እናቶች እርምጃው በጣም ጥሩ እንደሆነ ሲገልፁ ስድስት ወር ጡት ከማጥባት አንፃር አሁንም የወሊድ ፈቃድ ሊሻሻል እንደሚገባ የሚናገሩም አሉ።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ የማህፀንና ፅንስ ሃኪሞች ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ደረጀ ንጉሴ ከእናቶች ከወሊድ ማገገም እንዲሁም ስድስት ወር ከማጥባት አንፃር ማህበራቸው የወሊድ ፍቃድ መርዘምን እንደሚደግፍ ይናገራሉ።

ይህ ማለት ፍቃዱ ከዚህም በላይ ከፍ ቢል እንደ ህክምና ባለሙያ የሚደግፉት ነው።

በተቃራኒው በአገሪቱ ነባራዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ የወሊድ ፍቃድን መጨመር የሴቶችን ሥራ የመቀጠር እድል ይቀንሳል የሚል አስተያየት የሰጡን ሴቶችም አሉ።

በፌስቡክና በተለያዩ ገፆች ሴቶችን የሚመለከቱ ነገሮችን የምትፅፈው ቤተልሄም ነጋሽ ቀደም ሲል የወሊድ ፈቃድ እንዲጨመር በማህበራዊ ድረ ገፆች ቅስቀሳ እናድርግ የሚል ጥያቄ ቀርቦላት የነበረ ቢሆንም፤ መጀመሪያ የኢኮኖሚው ሁኔታና የቀጣሪዎች አመለካከት ከግምት ውስጥ መግባት አለበት ብላ በማመን በቅስቀሳው ከመሳተፍ መቆጠቧን ትናገራለች።

“ማህበረሰቡ መጀመሪያ መውለድ ዘር መተካት መሆኑን በመረዳት በወሊድ ምክንያት እናቶች ላይ የሚፈጠረውን ጫና ለመካፈል ፈቃደኛ መሆን አለበት። የድርጅት ባለቤቶች የወሊድ ፍቃድ ሲሰጡ ቀጣዩን ትውልደ እየተንከባከቡና እያሳደጉ መሆኑን ማወቅ አለባቸው” ትላለች።

የቀድሞዋ ጋዜጠኛ ሮዝ መስቲካ ሥራዋን ያቆመችው የመጀመሪያ ልጇን ስትወልድ እንደነበር ታስታውሳለች።

የወሊድ ፍቃድ ስድስት ወር መሆን አለበት በማለት በማህበራዊ ድረ ገፅ ቅስቀሳ ስታደርግ በመቆየቷ በአዋጁ መሻሻል ደስተኛ መሆኗን ትናገራለች።

“ስድስት ወር ይጨመር የምለው አንድም ስድስት ወር ለማጥባት፤ ሌላው ደግሞ እናት በቂ እረፍት እንድታደርግ ነው። ቢሆንም ግን የተገኘው አንድ ወርም ቀላል ባለመሆኑ ደስተኛ ነኝ። ብዙ እናቶች እንደሚያደርጉት ከራሳቸው ፍቃድ ጨምረው ስድስት ወር ሊያጠቡ ይችላሉ” ብላለች።

በመጀመሪያው የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ 515/1999 መሰረት የወሊድ ፍቃድ ሦስት ወር ነበር።

Advertisement