የመንግስት ሰራተኞች የወሊድ ፈቃድ ወደ አራት ወር ከፍ አለ – Maternity Leave

                                                               

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሻሻለውን የመንግስት ሰራተኞች ረቂቅ አዋጅ አጸደቀ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ስብሰባ የተሻሻለውን የመንግስት ሰራተኞች አዋጅን ጨምሮ ሌሎች ሁለት አዋጆችንም አፅድቋል።
የተሻሻለው የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ሀገሪቷ ከደረሰችበት የዕድገት ደረጃ ጋር የተጣጣመና የመንግስት ሰራተኛውን መብት የሚያስጠብቁ ድንጋጌዎችን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።
የሰው ኃብት ልማት እና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ረቂቅ አዋጁን በዝርዝር በማየት የውሳኔ ሀሳባቸውን ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
በዚህም ረቂቅ አዋጁ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታዩ ምርጥ ተሞክሮዎችን መሰረት ያደረገና አገሪቷ እያስመዘገበች ያለውን ዕድገት ማስቀጠል የሚያስችል ፐብሊክ ሰርቪስ ለመገንባት የሚረዳ መሆኑን የቋሚ ኮሚቴዎቹ በውሳኔ ሀሳባቸው አብራርተዋል።
የመጀመሪያው የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ 515/1999 በትግበራ ወቅት ያጋጥሙትን ችግሮች የሚፈታ እና አዋጁ የነበሩበትን ክፍተቶች የሚሞላ መሆኑም ተብራርቷል።
የተሻሻለው አዋጅ ለሴት ሰራተኞች የአራት ወራት የወሊድ ፍቃድ ከመስጠቱም ባለፈ በመንግስት መስሪያ ቤቶች የህጻናት ማቆያ ቦታዎች እንዲዘጋጁ የሚያደርጉ ድንጋጌዎችን ይዟል።
በቀድሞው አዋጅ የወሊድ ፍቃድ 90 ቀናት ወይም 3 ወር የነበረ ሲሆን፥ በተሻሻለው አዋጅ ወደ 120 ቀናት ወይም 4 ወር ከፍ ብሏል።
የወሊድ ፈቃዱ ፅንስ የተቋረጠባቸው ሴቶችንም የሚያካትት መሆኑ ተገልጿል።
አንድ የመንግስት ሰራተኛ የዓመት ፍቃድ በገንዘብ ሲለወጥ የሰራተኛው የአንድ ቀን ደመወዝ የሚታሰበው ያልተጣራ የወር ደመወዙን በ30 ቀናት በማካፈል መሆኑንም አዋጁ ይደነግጋል።
በሌላ በኩል የህመም ፈቃድ የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ከሙሉ ደመወዝ ጋር፣ለተከታዮቹ ሶስት ወራት ደግሞ ከግማሽ ደመወዝ ጋር እንዲሁም ለሚቀጥሉት ሁለት ወራት ያለደመወዝ እንደሚሰጥ ነባሩ አዋጅ ይደነግጋል።
በአዲሱ አዋጅ ግን የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ከሙሉ ደመወዝ ጋር፣ ለተከታዮቹ ሁለት ወራት ደግሞ ከግማሽ ደመወዝ ጋር እንዲሰጣቸው በሚል ተሻሽሏል።
የምክር ቤቱ አባላት አዋጁ አገሪቷ አሁን ከደረሰችበት የዕድገት ደረጃ ጋር የሚጣጣምና የመንግስት ሰራተኞችን መብት የሚያስጠብቁ ድንጋጌዎችን ያካተተተ ነው በማለት በአንድ ድምፀ ተአቅቦና በአብላጫ ድምፅ አፅድቀውታል።
ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው የተፈጥሮ ኃብት ልማትና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የደን ልማት ጥበቃና ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ያቀረበወን የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ በአብላጫ ድምፅና በ13 ድምፀ ተአቅቦ አፅድቋል።
በኢትዮጵያ መንግስትና በአለምአቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለፍትሃዊ የመሰረታዊ አገልግሎቶች ማስፋፊያ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የሚውል ተጨማሪ ብድር ለማግኘት የተደረገውን ስምምነት ለማፅደቅ የቀረበ ረቂቅ አዋጅንም በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ

Advertisement