መፍትሄ ያልተገኘለት የሞያሌ ጉዳይ – Unresolved Crisis in Moyale

                                                         

የሞያሌ ነዋሪዎች በፍርሃት እና በሽብር መኖር ከጀመሩ ረዥም ጊዜያት ተቆጥረዋል።

ሊያድግ እና ሃገሪቱን ሊጠቅማት የሚገባው የድንበር ከተማዋ ኢኮኖሚ ከመጎዳት ባለፈ ችግር ውስጥ ገብቷል።

በቅርቡም ህዳር 12/2010 ጸሃይዋ ገና ብቅ ከማለቷ ነበር ኢትዮጵያን ከኬንያ በሚያገናኘው ዋና መንገድ ላይ በሶማሌ እና ኦሮሞ ወጣቶች መካከል ግጭት የተፈጠረው።

በድንጋይ እና በዱላ የታገዘውን ግጭት በአካባቢው የነበረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ደርሶ አስቁሟል። ይህን ተከትሎ ሞተር ሳይክሎችም በከተማው ውስጥ እንዳይንቀሳቀሱ ተደርጓል።

ከደቂቃዎች በኋላ ከተማዋ “ወደ ተለመደው” ሁኔታ የተመለሰች ሲሆን የንግድ እንቅስቃሴውም ተጀምሯል።

በዚህች የድንበር ከተማ ቀደም ሲል በግጦሽ እና በውሃ ምክንያት በአርብቶ አደሮች መካከል ግጭት መከሰቱ የተለመደ ነበር።

እንዲህ ያሉ ግጭቶቹን በባህላዊ ሽማግሌዎች እና አባ ገዳዎች ከመፍታት ባለፈ ጉዳት ለደረሰባቸውም ካሣ ክፍያ ሲፈጸም ቆይቷል።

በሞያሌ የሚኖሩ ሃገር ሽማግሌዎች እንደሚሉት ከሆነ አሁን የሚከሰቱት ግጭቶች ብሄር ተኮር እየሆኑ በመምጣታቸው ከ1990ዎቹ የተለዩ ናቸው።

በሞያሌ ተወልደው ያደጉት አቶ ተቼ አዴኖ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በከተማዋ የሚስተዋሉት ግጭቶች እና የደህንነት ችግሮች ምክንያታቸው ከተማዋ የምትተዳደርበት የአስተዳደር ስርዓት ነው።

አቶ ተቼ በሞያሌ ያለውን ጉዳይ ሁለት ባል ካላት ሚስት ጋር ነው ያነጻጸሩት። “አንዲት ሴት ከሁለት ባሎች ጋር አትኖርም። ይህ ነው በሞያሌ እየተከሰተ ያለው” ይላሉ።

ከምስረታ ወደ ህዝበ ውሳኔ

በሞያሌ ከተማ ሁሉም ነገር ጥንድ ጥንድ ሆኖ ነው የሚገኘው።

በከተማዋ የአስተዳዳር ቢሮዎች፣ የፖሊስና የጤና ተቋማት እና ሌሎች የመንግሥት ቢሮዎች ሁለት ሁለት ናቸው።

በዋናው መንገድ ግራ እና ቀኝ የሁለቱም ክልል መንግሥታት የክልላቸውን እና ፌደራል መንግሥቱን ሰንደቅ ዓላማ ሰቅለዋል።

ከተማዋን ለሁለት ሰንጥቆ የሚያልፈው ዋናው መንገድ ሁለቱን ክልላዊ መንግሥታት የሚለየው ድንበር ተደርጎ ቢወሰድም አብዛኛዎቹ የኦሮሚያ መንግሥት መስሪያ ቤቶች የሚገኙት በሶማሌ ክልል በኩል ነው።

የሶማሌ ክልልም አንዳንድ ቢሮዎች በኦሮሚያ ክልል ውስጥ አሉት።

                                                   

አጭር የምስል መግለጫአቶ ቦሩ ሮባ በሞያሌ ከተማ ለ74 ዓመታት ኖረዋል

“ሞያሌ ከተማ በሁለት ክልሎች ነው የምትተዳደረው፤ አንዱ ክልል አንድ ነገር ሲሰራ ሌላኛው አይሰራም፤ ይህ ችግር ላለፉት 27 ዓመታት ሲከሰት ቆይቷል፤ ስለጉዳዩ ብዙ ጊዜ ቅሬታ ብናቀርብም መፍትሔ አልተሰጠውም” ይላሉ የ74 ዓመቱ አቶ ቦሩ ሮባ።

አስሊ ሃደሮ የተባሉት እናት ቤታቸው ከተቃጠለባቸው ሰዎች አንዷ ናቸው። ከቻሙክ ቀበሌ ከአራት ልጆቻቸው ጋር ተፈናቅለዋል። ባለፉት ሶስት ወራት ከመንግሥት 20 ኪሎ የስንዴ ዱቄት ብቻ እንዳገኙ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ከአዲስ አበባ በ775 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ሞያሌ በ1909 ነበር ህጋዊ ዕውቅና አግኝታ ከተማ የሆነችው።

እንደ የድንበር እና የንግድ ከተማነቷ የተለያዩ ብሔርና ብሔረሰቦች በጋራ ይኖሩባታል።

ሆኖም ፌደራላዊ የመንግሥት አደረጃጀት ይፋ ከተደረገ በኋላ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ እየተነሳ በሞያሌ እና በአካባቢው በሚኖሩ ብሄርና ብሄረሰቦች መካከል ግጭቶች መፈጠር ጀመሩ።

የነበረውን የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ለመመለስ የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት የጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት 11 ቀበሌዎችን ለሶማሌ ክልል ሲሰጥ 17 ቀበሌዎችን ደግሞ ለኦሮሚያ ክልል ሰጥቷል።

ይህ ውሳኔ ግን በሞያሌ ከተማ ያለውን ችግር በጥቂቱ ብቻ ነበር የፈታው።

በ2004 የተካሄደው ህዝበ ውሳኔ በሽግግር መንግሥቱ ምላሽ ያልተሰጣቸውን ጉዳዮች እንደሚፈታ ታምኖበት ነበር።

ህዝበ ውሳኔው በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልል ድንበር አካባቢዎች የሚገኙ 463 ቀበሌዎችን ዕጣ ፈንታ ለመወሰን የታሰበ ነበር። በሁለቱ ክልል መንግሥታት አለመግባባት ምክንያት ግን ህዝበ ውሳኔው በሞያሌ ሳይካሄድ ቀርቷል።

በዚህ ምክንያትም በሞያሌ ከተማ የሚገኙ ስምንት ቀበሌዎች ሠላም ያጡ ሲሆን “የጦርነት ቀጠና” ሆነዋል።

መፈናቀል፣ ታሪክ እና መፍትሔ

በኢትዮጵያ እና በኬንያ ሞያሌ እንዲሁም ኢትዮጵያ ውስጥ በሶማሌዎች እና በኦሮሞዎች መካከል በሚነሳ የድንበር ግጭት የብዙዎች ህይወት ጠፍቷል።                                                                               

አጭር የምስል መግለጫከቻሙክ ቀበሌ ተፈናቀሉ ሰዎች የሰሩት የላስቲክ ቤቶች

በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቀያቸው ሲፈናቀሉ በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመገመት ይከብዳል።

በሶማሌዎች እና በኦሮሞዎች መካከል በቅርቡ በተከሰት ግጭት 54 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል ሞያሌ አካባቢ ተፈናቅለዋል።

ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ በሶማሌ በኩል የዞኑን የደህንነትና አስተዳደር ኃላፊና የክልሉን የመንግሥት የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ለማናገር ቢሞክርም በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

በግጭቶቹ ምክንያት የከተማዋ ኢኮኖሚም እየተጎዳ ይገኛል።

ምግብ እና ሌሎች ቁሳቁሶችን ወደ አካባቢው ለማምጣት የትራንስፖርት ችግር ስላለ በሞያሌ እና በአካባቢው የምግብ እና የሌሎች ሸቀጦች ዋጋ ጨምሯል።

የሞያሌ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ቦሩ ሮባ እንደሚያምኑት ከሆነ ስር ለሰደደው የሞያሌ ከተማ ችግር ጥሩ የሚባልው መፍትሔ ከህዝበ ውሳኔ ይልቅ የታሪክ ምላሽ ነው።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement