“ሶስት ጊዜ ለተለያዩ ነጋዴዎች ተሽጫለሁ” – “I Have Been Sold Three Times “

                                               

ሀሩን አህመድ የሰሃራ በረሃን በማቋረጥ ወደ ሊቢያ ከዚያም ወደ አውሮፓ ለመግባት ጥረት ከሚያደርጉ በርካታ ኢትዮጵያውን ስደተኞች መካከል አንዱ ነው።

አሁን ጀርመን ሀገር የሚኖረው የ27 ዓመቱ ሀሩን በስደት ጎዞው ላይ “ከአንድም ሶስት ጊዜ እንደባሪያ ተሽጫለሁ” ሲል ያጋጠመውን አጫውቶናል። እጅግ አስደናቂ የሆነውን የሀሩንን የስደት ጉዞ ከራሱ አንደበት እነሆ…

በባሌ ዞን ውስጥ አጋርፋ በሚባል ቦታ ነው የተወለድኩት። ከሀገር እንድወጣ ያደረገኝ ዋናው ምክንያት የተሻለ ህይወት ፍለጋ ነው። መዳረሻዬን አውሮፓ ለማድረግ የስደት ጉዞዬን የጀመርኩት እአአ በ2013 ዓ.ም ነበር።

የመጀመሪያ ጉዞዬ ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን ነው ነበር ያደረኩት። በሱዳን ለጥቂት ጊዜ ከቆየው በኋላ ከሌሎች ስደተኞች ጋር በመሆን ለሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች በነብስ ወከፍ 600 ዶላር በመክፈል ጉዞ ወደ ሊቢያ ተጀመረ።

የሊቢያ ጉዞ የተጀመረው በጭነት መኪና ነበር። አስታውሳለሀሁ በዛ መኪና ላይ ከ98 በላይ የምንሆን ሰዎች ተጭነን ነበር። የአካባቢው ሙቀት፣ የውሃ ጥማት እና ረሃቡ እንዲሁም እርስ በርሳቸውን ተደራርበን እንደመጫናችን ጉዞው አድካሚ ብቻ ሳይሆን ተስፋ አስቆራጭ ነበር።

ይህ አስከፊ የበረሃ ላይ ጉዞ ለስድስት ተከታታይ ቀናት ቀጠለ። በስድስተኛው ቀን ግብፅን፣ ሊቢያን እና ቻድን የሚያዋስን ቦታ ላይ ደረስን።

ይህ ቦታ ህገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪች ስደተኞችን የሚቀባበሉበት ስፍራ ነው።

ቦታው ላይ የደረስነው እጅግ ተጎሳቁለን እና ተዳክመን ነበር። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ያላሰብነው ነገር ገጠመን። ድንገት የታጠቁ ሰዎች መጥተው የነበረንን ገንዘብ እና ከሌሎች ላይ ወርቅ ሌሎች ጌጣ ጌጦችን ዘርፈውን ሄዱ።

                                                               

‘የሰው ልጅ አይመስሉም’

ወደ ስፍራው የወሰዱን ሰዎች ለሊቢያ ደላሎች አሳልፈው ሊሰጡን ነበር ይሁን እንጂ በመሃል ባለወቅነው ምክንያት ሌሎች ደላሎች አስገድደው ወደ ቻድ ወሰዱን። አሁንም አሰልቺ እና ተስፋ አስቆራጭ የሆነ የሁለት ቀን ጉዞ ካደረግን በኋላ ቻድ ውስጥ የሚገኝ አንድ ካምፕ ውስጥ አስገድደው አንድንገባ አደረጉን።

አሳሪዎቻችን አረብኛ እና ሌሎች የማላውቃቸውን ቋንቋዎች ስለሚናገሩ ምን እንደሚሉ አናውቅም ነበር።

ከቀናት በኋላ አንድ መኪና አመጡና “4000 ዶላር መክፈል የምትችሉ እዚህ መኪና ውስጥ ግቡ የማትችሉ ግን እዚሁ ቁጭ በሉ” ሲሉ አዘዙን።

በጊዜው የጠየቁት ገንዘብ በምንም ተዓምር ሊኖረኝ አይችልም ሆኖም ግን በካምፑ ውስጥ መቆየት እጅግ አስጨናቂ ስለነበር የጠየቁት ገንዘብ እንዳለኝ በማስመሰል ተስማምቼ ተሳፈርኩ። እኔ ብቻ ሳልሆን ሌሎች በርካታ ስደተኞች ገንዘብ ያላቸው በማስመሰል መኪናው ላይ ወጡ።

ወዴት እንደሚወስዱን እንኳን እርግጠኛ ሳንሆን ከሶስት ቀናት ጉዞ በኋላ ከአንድ ስፍራ ደረስን።

አሳሪዎቻችን ያመጡን ስፍራ ስደተኞች የሚሸጡበት ቦታ መሆኑን የተረዳነው ግን ዘግይተን ነበር።

ወደስፍራው ያመጡን ሰዎች ለሌሎች አዘዋዋሪዎች አሳልፈው ሰጡን።

የተቀበሉን ሰዎች ደግሞ እያንዳንዳችንን በ4000 ሺህ ዶላር እንደገዙን ከነገሩን በኋላ ሁለችንም ገንዘቡ ካልከፈልናቸው እንደማይለቁን አሳወቁን።

እዛ ያገኘናቸው ከኤርትራና ሶማሊያ የመጡ ስደተኞች የተጠየቁትን ገንዘብ መክፈል ባለመቻላቸው አምስት ወር ያህል መቆየታቸውን ነገሩን። ከዛም ስደተኞቹን አሳዩን። ልጆቹ በጣም ከመጎሳቆላቸው የተነሳ የሰው ልጅ እንኳን አይመስሉም ነበር። እጅግ በጣም የፍርሃት ስሜት ሰውነቴን ወረረው።

የተጠየቀውን ገንዘብ መክፈል ያልቻልነው የኤርትራና ሶማሊያ ስደተኞች ዕጣ ደረሰን። ያሰቃዩን ጀመር። ገንዘብ እንደሌለኝ በተደጋጋሚ እየተማጸንኩ ብነግራቸውም ለአፍታ እንኳን ሊሰሙኝ ፍቃደኛ አልነበሩም።

በቀን አንድ ጊዜ መጠኑ በጣም አነስተኛ የሆነ ምግብ ይሰጡናል። ቶሎ እንዲርበን ደግሞ ጋዝ ከውሃ ጋር እየቀላቀሉ እንድንጠጣ ያደርጉናል። ከጋዝ ጋር የተቀላቀለ ውሃ መጠጣት በጣም ያስርባል። እንደዛም ሆኖ ስለሚጠማን እንጠጣው ነበር። ሁልጊዜ ማታ ማታ እየመጡ ያሰቃዩንም ነበር። ይህን ሁሉ ስቃይ የሚያደርሱብን የጠየቁትን ገንዘብ ቶሎ እንድንከፍላቸው በማሰብ ነበር።

‘ቀጫጫ ሰው ዋጋ አያወጣም’

ከቤተሰቦቻቸው ገንዘብ የተላከላቸው የተወሰኑ ኤርትራዊያንና ሶማሊያውያን የተጠየቁትን ከፍለው መሄድ ቻሉ። እኔን ጨምሮ 32 ኢትዮጵያውያን ግን ምንም ገንዘብ ስላልነበረን ለተጨማሪ 80 ቀናት ቆየን።

ከሁለት ወር በላይ በአስከፊ ሁኔታ ስለቆየን በጣም ገርጥተን እና ተጎሳቁለን ነበር። ሰዎቹም “ገንዘባችንን ልትከፍሉን ስለማትችሉ ልንሸጣችሁ ነው” ሲሉ ነገሩን።

ከጥቂት ቀናት በኋላ አንድ ሰውዬ ሊገዛን እንደመጣ ሰማን። ሊገዛን የመጣው ሰውየም በአትኩሮት ተዘዋውሮ ከተመለከተን በኋላ ‘እነዚህ ኩላሊታቸው እንኳን ሊጠቅም አይችልም’ ብሎ ተመለሰ።

ትንሽ ቀን ቆይቶ ደግሞ አንድ ሌላ ገዢ ሳባ ከተባለ የሊቢያ አካባቢ መጥቶ እያንዳንዳችንን በ3000 ሺህ ዶላር ገዛን። ስውየው ወደ መኪናው እየወሰደን በፍፁም ያሳለፍነውን ዓይነት ችግር እንደማይደርስብን ቃል ግበቶልን ይዞን ሄደ።

ነገር ግን ከአራት ቀናት ጉዞ በኋላ የደረስንባት ‘ሳባ’ የምትባለዋ አካባቢ እጅግ ኢ-ሰብዓዊ የሆነ ስቃይ ደረሰብን።

አጆቻችን የኋሊት ካሰሩን በኋላ ፊታችንን በላስቲክ በማፈን በውሃ የተሞላ በርሜል ውስጥ እየከተቱ እና እያወጡ አሰቃዩን።

ሁሉም ነገር ከአቅሜ በላይ ሆነብኝ። ሞት ናፈቀኝ። ለአንድ ወር ያህል የተለያዩ ስቃዮችን አደረሱብን።

በዚህ መሃል ከመሃከላችን ጥቂቶቻችን ቤተሰቦቻችን በስልክ አገዕነንተን 3000 ዶላር እንዲልኩልን አድርገን ከፍለን ከዛ ቦታ መውጣት ቻልን።

ቦታውን ለቀን ብዙም ሳንጓዝ ሌሎች ሰዎች መጥተው አፍነውን ወደ ሌላ ማጎሪያ ስፍራ ወሰዱን። ስቃይና ድብደባው እንደአዲስ በረታብን። እጅግ በጣም ተስፋ አስቆራጭ ነበር። አሁንም ቤተሰብ ጋር ደውለን 1000 ዶላር ካስላክን በኋላ እሱን ከፍለን መውጣት ቻልን። የግመሾቻችን ቤተሰቦች ከብት፤ የተቀረው መሬት፤ ብቻ ያላቸውን ነገር ሸጠው ከመከራ አወጡን።

                                                 

የጥገኝነት መብት

ቀጣይ መዳረሻችን ‘ትራቦሊስ’ የምትባል ስደተኞች በብዛት የሚኖሩባት የሊቢያ አነስተኛ ከተማ ነበረች። እዛ ያለው ሁኔታ በንፅፅር ካየናቸው ቦታዎች የተሻለ ነበር። ትራቦሊስ ከተማ ለተወሰኑ ወራት ያክል ያገኘነውን እየሰራን እራሳችንን ለሌላ ጉዞ ማዘጋጀት ጀመርን።

ሜድትራኒያን ባሕርን ለማቋረጥ ዝግጅት ጀመርን። ለጉዟችን አስፈላጊ የሆኑት ዝግጅቶችን አደረግን። ሜድትራኒያን ባሕር ላይ በፖሊስ ከተያዝን ለሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች እስከ 500 ዶላር ድረስ ልንሸጥ እንደምንችልም እናውቃለን።

ጉዞ ጀመርን። ፈጣሪ ምስጋና ይግባውና ክፉ ነገር ሳይገጥመን ጣሊያን ገባን። እኔም በጣሊያን በኩል አድርጌ ጀርመን መግባት ቻልኩ።

ከጀርመን መንግሥት ሕጋዊ የጥገኝነት መብት በማግኘቴ የተሻለ ቦታ ላይ ብገኝም ያሳለፍኩትን ስቃይና መከራ ግን በፍፁም አልረሳም።

እኔ በህይወት ተርፌ እዚህ ልድረስ እንጂ በግብፅና ሊቢያ ወደብ አካባቢ አንድ ጓደኛችንን ቀብረናል። ሁለት ጓደኞቻችን ሳባ የተባለችው የሊቢያ ከተማ ቀርተዋል። ይሙቱ ይኑሩ የማውቀው ነገር የለም። ሌላ አንድ የማውቃት ልጅ ደግሞ ሜድትራኒያን ባሕር ውስጥ ሰምጣለች። እኔና የተወሰንን ዕድለኞች ነን ሕይወታችንን ይዘን አውሮፓ መግባት የቻልነው።

እውነት ለመናገር ሃገሬን ጥዬ ስወጣ የስደት ሕይወት በፍፁም እንዲህ አሰቃቂ ይሆናል ብዬ አላሰብኩም። ይህንን ባውቅ ትምህርቴን ላይ ትኩረት በማድረግ እቀጥል ነበር ወይ ደግሞ ሥራዬን አርፌ እሠራ ነበር። ነገር ግን የተሻለን ህይወት ፍለጋ ብዙ ሰዎች ሀገር ጥለው ሲወጡ እመለከታለው ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በሃገሪቱ ውስጥ ያለው ማሕበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ለስደት የሚዳርጉ ናቸው።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement