በአሁኑ ጊዜ በኢንተርኔቱ ዓለም እጅግ በጣም ፈጣን የተባለውን ኔትዎርክ ይዘው ለመቅረብ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በመፎካከር ላይ ይገኛሉ።
ይህንን ፉክክር በቅርቡ ለመቀላቀል ካቀዱት ውስጥ ኢንቴል እና አፕል ተጠቃሽ ሲሆኑ፥ ኳልኮም፣ ኤሪክሰን፣ ኖኪያ እና መሰል ኩባንያዎች ደግሞ ኔትዎርኩን ወደ መስራት ከገቡ ዋል አደር ብለዋል።
ኤሪክሰን የተባለው ኩባንያ ደግሞ የዓለማችን ፈጣኑ የተባለውን የ5G ኔትዎርክ በህንድ መሞከሩ እየተነገረ ነው ያለው።
ኤሪክሰን የ5G ኔትዎርክን ወደ ህንድ ለማስገባት ከህንዱ ባሃርቲ ኤርቴል የቴሌኮም ኩባንያ ጋር ከስምምነት ላይ መድረሱም ተገልጿል።
በስምምነቱ መሰረትም ኤሪክሰን ከህንዱ ግዙፍ የቴሌኮም ኩባንያ ጋር በቀጣይ በህንድ በሚኖረው የ5G ኔትዎርክ ግንባታ ዙሪያ በጋራ የሚሰሩ ይሆናል ተብሏል።
ኤሪክሰን ከዚህ በፊትም የ4G ኔትዎርክ መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ዙሪያ ከህንዱ ባሃርቲ ኤርቴል የቴሌኮም ኩባንያ ጋር መስራቱም ተጠቅሷል።
ስምምነቱን ተከትሎም ኤሪክሰን የመጀመሪያውን የ5G ኔትዎርክ ሙከራ ማድረጉም ተነግሯል።
ሙከራውም በሰከንድ የ5 ነጥብ 7 ጊጋ ባይት ፍጥነት እንደነበረው ታውቋል።
እንደ ኤሪክሰን ገለፃ የ5G ኔትዎርክ ቴክኖሎጂ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2026 ለህንድ 27 ነጥብ 3 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)