የቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት ትውስታዎች በኢትዮጵያውያን ዓይን – Soviet Union Memories

                                                          

ሶስትና አራት አስርት ዓመታትን ወደ ኋላ ብንሄድ የኢትዮጵያን የስነ-ፅሁፍ ስራዎች በሩሲያ ወይም በቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት ፀሀፊያን የትርጉም ስራዎች የተሞላ ነበር።

ከነዚህም ውስጥ የፊዮዶር ዶስቶቭስኪ ‘ክራይም ኤንድ ፐኒሽመንት’ የሚለው ፅሁፍ ወንጀልና ቅጣት በሚል ርዕስ በሩሲያ አምባሳደር በነበሩት ካሳ ገብረ-ህይወት ተተርጉሟል።

የዚሁ ደራሲ ስራ የሆነው ‘ኖትስ ፍሮም አንደርግራውንድ’ የስርቻው ስር መጣጥፍ በሚል የማክሲም ጎርኬይ እናት እንዲሁም የሊዮ ቶልስቶይ ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው። በፅሁፋቸውም ስለ ሩሲያ አብዮት፤ ስለ ጭቆናና መደብ ትግል፤ ወይም ታዋቂ ስለሆነው ሬድ ስኩዌር (አደባባይ)ም ይሁን ስለ አጠቃላይ ባህሉ ጠቅሰዋል።

በአድዋ ጦርነትም ይሁን ለሁለተኛ ጊዜ ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ድጋፍ ወደሰጠቻት የቀድሞ ሶቭየት ህብረት ብዙ ተማሪዎች በ1960ዎቹና በ1970ዎቹ ሄደዋል። በተለይም ዓለም አቀፍ ሶሻሊዝም በተስፋፋበት ወቅት የሶቭየት ህብረትና የኢትዮጵያ ግንኙነት ጠንካራ ነበር።

የሶሻሊዝምን ርዕዮተ-ዓለም የሚያንፀባርቁት የካርል ማርክስ፣ የቭላድሚር ሌኒን ሀውልቶች፤ የኮሚዩኒስት ማኒፌስቶ ትርጉም በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠቀሱ ናቸው።

በዚያን ወቅት የቀድሞ ሶቭየት ህብረት ሄደው ከተማሩት ውስጥ ታዋቂው ፀሐፊ-ተውኔት አያልነህ ሙላቱ ይገኙበታል። አያልነህ የትያትር ድርሰትን ለመማር ወደ ሞስኮ ያቀኑት በንጉሱ ዘመን በ1962 ዓ.ም ነበር።

በወቅቱ በአሜሪካ የትምህርት ዕድል የነበረ ቢሆንም ከደራሲያን ማህበር መንግስቱ ለማ “ገንዘብን ለማካበት ከሆነ በካፒታሊዝም ወደ ምትመራዋ አሜሪካ ብሄድ ጥሩ እንደሆነ ነገር ግን ስነ-ፅሁፍን ለመማር ከሆነ ወደ ሶቭየት ህብረት ብሄድ ጥሩ እንደሆነ መከሩኝ” በማለት ይናገራሉ።

ቦታው ላይ ሲደርሱ የአሌክሳንደር ፑሽኪን አያት ኢትዮጵያዊ/ኤርትራዊ ከመሆን ጋር ተያይዞ በክብር እንደተቀበሏቸው ያስታውሳሉ። ፀሀፊና ገጣሚ መሆናቸውም ከእሱ ጋር በከፍተኛ ሁኔታ በመያያዙ ሞስኮ በሚገኝ ሬድዮ በሳምንት ሁለት ጊዜ “የደራሲው ደብተር” በሚል ርዕስ በአማርኛ የሬድዮ ፕሮግራም ያቀርቡ ነበር።

ፑሽኪን ስለ አያቱ “ዘ ኒግሮ ኦፍ ፒተር ዘ ግሬት” በሚለውም ፅሁፉ አስቀምጧል።

በኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴ በሶሻሊዝም፣ኮሚዪኒዝምና ማኦይዝም ርዕዮተ-ዓለም በተዋጠበት ወቅት የሶሻሊዝም ሀገራት የኑሮ ሁኔታ ምን እንደሆነ መሬት ላይ ያሳያቸው ሁኔታ እንደሆነ ይናገራሉ።

“የሶቭየት ህብረት ሶሻሊዝም ሰዎችን የማያበላልጥ፤ የሰዎችንም ክብርም ከፍ የሚያደርግ ስርአት ነው” በማለት ይናገራሉ።

በቦታው ሲደርሱ በጣም ያስደነቃቸውም የማህበራዊ አኗኗራቸው ነው። እንደ ኢትዮጵያ አይነት ከፍተኛ የማህበራዊ ኑሮ ትስስር ካለበት ቦታ ቢመጡም የሩሲያ ከማስደነቅም በላይ ነበር የሆነባቸው።

“የግል ንብረት የሚባል የለም” የሚሉት አያልነህ በመጀመሪያ በመጡበትም ወቅት ሸሚዛቸውን ያለሳቸው ፈቃድ ለብሶ ያገኙትን ተማሪ ተናደው ሊጣሉት ባሉት ወቅት “ለምን እንደተናደድኩ አልገባውም፤ የኔ ልብስ እኮ ስላልታጠበ ነው፤ ሲታጠብ ትለብሳለህ” ብሏቸዋል።

የካፒታሊዝም ዋና ፅንሰ-ሀሳብ የሆነውን “የሀብት ክምችትን” በመቃወም “ለነገ የሚያስቀሩት ነገር የለም” ይላሉ። ማንኛውም የሰው ልጅ መሰረታዊው ነገር ሊሸፈን ይገባል በሚለው መርሀቸው መሰረት ምግብ ርካሽ ከመሆኑ በተጨማሪ ህክምናና ትምህርት በነፃ እንደነበር ይናገራሉ።

ኑሮ በሞስኮ ቀላል አልነበረም ምክንያቱም እንደ አቶ አያልነህ ሀይማኖት አጥባቂና ከፊውዳሊዝም ስርዓት የመጣ ሰው መደብ የሌለበትና እምነት እንደ ማርክስ አባባል ኦፒየም (ማደንዘዣ) የሚታይበት ሁኔታ ቀላል አልነበረም።

በወቅቱም የሩሲያ አብዮት አመላካች የሆነችውን የቀይ ኮከብ አርማን “ኮከቧ ወደ እግዚአብሄር እያመላከተች ነው” በማለታቸው ብዙዎችን እንዳስደነገጠም አይዘነጉትም። ምንም ባይደርስባቸውም እምነትን እንዲህ ባደባባይ ላይ መናገር ፍፁም ክልክል እንደነበር ይናገራሉ።

በወቅቱም ብዙ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ስለነበሩ ማህበር የነበራቸው ሲሆን የአውሮፓ ተማሪዎች ማህበር አባል ነበሩ። “የሶሻሊዝሙ ዕምብርት ላይ ስለነበርን ማዕከልም ነበርን” ይላሉ።

ሞስኮ ውስጥ እንጀራም ይሁን የኢትዮጵያ ሬስቶራንት ባይኖርም አብዛኛውን ጊዜ ከማርክስ ሀውልት አጠገብ ያለው ሬድ ስኩዌር የተባለ አደባባይ እንዲሁም ፑሽኪን አደባባይ እንደሚሄዱም ይናገራሉ።

ስለ ደግነታቸው አውርተው የማይጠግቡት አያልነህ ልጃቸው ሩሲያ ከተወለደ በኋላ ይንከባከቡላቸው የነበሩት “ባቡሽካ” (የሩሲያ አያቶችንም) በእጅጉ ያስታውሳሉ። አሁንም የእርጅና ጊዜያቸውን እዛው ቢያሳልፉ ደስ እንደሚላቸው ይገልፃሉ።

                                                        

ከአቶ አያልነህ በ20 ዓመታት ልዩነት የሄዱት የስነ-ጥበብ መምህርና ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን ልምድ ከዚህ በተቃራኒው ነው። የሶቭየት ህብረት መፈራረስ ዋዜማ ላይ የሄዱት በቀለ መኮንን ታላቅ እየተባለ ሲሞካሽ የነበረው ሶሻሊዝም በከፍተኛ ደረጃ በሚተችበት፤ “የግራ ፖለቲካ ጣኦቶቻቸውን መደርመስ የጀመረበት ጊዜ ነበር” በማለትም ይገልፃሉ።

ራሱን ሶሻሊስት ብሎ የሚጠራው የደርግ መንግስት “ብዙ ሰዎችን በማፈስ፣ በማሰር፣ በማንገላታት ላይ ስለነበር ወደ ሩሲያ መሄዱም አማራጭ ከማጣት ጋር ወይም ሽሽት ነው” ይላሉ።

መጀመሪያ ሞስኮ የገቡበትን ቀን የማይረሱት በቀለ “አጥንት ድረስ የሚሰማው ብርድ ሲሰማኝ፤ ብረት የማሸት ነው የመሰለኝ” ይላሉ።

በጊዜው ሶሻሊስት ተብላ ብዙ ጥፋት ካለባት አገር ወደ ሌላ ሶሻሊስት ሀገር መሄድ የነበረውን ስሜት ሲገልፁ “ሁሉን ነገር በጥርጣሬና በጥላቻ ነበር የምመለከተው፤ ሩስኪ በምማርበት ወቅት እንኳን የነበረኝን የእንግለዚዝኛ ቋንቋ ለማስጠፋትና ለማደናበር ይመስለኝ ነበር” ይላሉ።

“ህዝቡ በፍርሀት ከተሸበበት እየወጣ በነበረበት ሁኔታ ላይ ነው የደረስኩት” የሚሉት በቀለ ሶሻሊዝም የተተረጎመበት መንገድም ትክክል ነው ብለው እንደማያስቡም ይናገራሉ።

                                                                    

“ቤተ-ክርስቲያን የሚሄዱ ሰዎች ነፃ ህክምናም ሆነ ነፃ ትምህርት አያገኙም፤ ስለዚህ ሰዎች ተደብቀው ይሄዱ ነበር” ይላሉ። መሰረታዊ ነገሮች የተሟሉበት ሁኔታ እንዲሁም ምግብ እንደ ሰብዓዊ መብት ታይቶ የሚራብ ሰው ባይኖርም ስርዓቱን መቃወም አይቻልም ነበር በማለት በቀለ ያወሳሉ። “የተቃወሙ ብዙዎች ወደ ሳይቤሪያ ይጋዛሉ፤ ነፃነት አልነበረም” ይላሉ።

የነበረውን ስርኣት ከጆርጅ ኦርዌል “አኒማል ፋርም” ከተሰኘ ድርሰት ጋር የሚያመሳስሉት በቀለ በወቅቱ ይሰበክ የነበረውን የመደብ እኩልነትም ጥያቄ ውስጥ ይከቱታል።

“ባቡር ውስጥ ስንገባ ሰዎች ይገላመጣሉ፤ ስታሊን በዘረጋው የጠበቀ ስለላ መሰረት ሚስቶች ባሎቻቸውን የሚሰልሉበት መረብም ነበር። ብዙዎችም ወደ ሳይቤሪያም ተግዘዋል” ይላሉ።

የጅምላ አስተሳሰብ የሰፈነበት ስርዓት ነው ቢሉም የሥነ-ፅሁፍ ባህላቸው በጣም የመጠቀና የማንበብ ባህላቸው አስደናቂ እንደነበር ግን ሳያወሱ አያልፉም።

የቦሪስ የልሰንን መሪነትን ተከትሎ የሶሻሊዘም ዓለም አቀፍነት ተደምስሶ በጥቁር ህዝብ ላይ ያለው ዘረኝነት ጎልቶ ቢወጣም በዛን ጊዜ ግን በአደባባይ ዘረኝነት እንዳልነበር ይናገራሉ። “ጥቁር ሰው አይተው የማያውቁ ወይም አንዳንዶች በግዴለሽነት ቢያደርጉትም ብዙዎች ከሩሲያ ወዳጅ ስለመጣን ማስቀየም ይፈሩ ነበር” ይላሉ።

ምንም እንኳን በ6 አመት ቆይታቸው ሞስኮን ብዙ ባይወዱዋትም የሌኒን ግራድ፤ ዊንተር ፓላስ የመሳሰሉ አካባቢዎች ትዝታ አሁንም እንዳለ ነው።

ምንጭ: ቢቢሲ

 

Advertisement