ታሪክን የኋሊት – ለ28 ዓመታት ጀርመንን ለሁለት ከፍሎ የነበረው የጀርመን ግምብ ሲፈርስ – 28 Years The Fall of Berlin Wall

                                                                          

                                                               
                                                   

የኔነህ ከበደ

የበርሊን ግምብ በፍልስፍናና በአስተዳደር ዘይቤ የአንድ አገር ሰዎችን ለሁለት በመክፈል የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን የጥላቻ ግድግዳ ተደርጐ ይቆጠራል፡፡

ለዓመታት ጀመርኖችን ከፋፍሎ የቆየው ግንብ ክፍት ሆኖ ምሥራቅ ጀርመናውያን ወደ ምዕራቡ እንዲሻገሩ የተፈቀደላቸው የዛሬ 28 ዓመት በዛሬዋ ዕለት ነበር፡፡

የጀርመን ናዚዎች ዓለምን በመዳፋችን ውስጥ እናውላለን ብለው ከ78 ዓመታት በፊት ጦርነት አቀጣጠሉ፡፡ የኋላ ኋላ በተነሱበት ፍጥነት መቀጠል ተሳናቸው፡፡

በሌሎች ላይ የለኮሱት እሳት ራሳቸውን ማቃጠሉን ያዘው፡፡

የህብረቱ ኃይሎች ከየአቅጣጫው መጡባቸው፡፡ የአንግሎ አሜሪካ ኃይል ከምዕራብ፤ የሩሲያ ሠራዊት ከምስራቅ አቅጣጫ መጡባቸው፡፡ መፈናፈኛ አጡ፡፡

አገራቸው በህብረቱ ኃይሎች ተፅዕኖ ስር ወደቀች፡፡

ከጦርነቱ በኋላ ምዕራባዊ ክፍሏ በአሜሪካ፣ እንግሊዝና ብሪታንያ አስተዳደር ስር ሆነ፡፡ 
የምስራቃዊው ክፍል ደግሞ በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ተፅዕኖ ሥር ወደቀ፡፡

ምዕራባዊው ክፍል የጀርመን ፌዴራል ሪፐብሊክ ተሠኝቶ ራሱን ቻለ፡፡ የምስራቁም ግዛት ምስራቅ በርሊንን ርዕሠ ከተማው በማድረግ በሶቪየት ተቀጥላነት የጀርመን ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ተባለ፡፡

በዚያን ጊዜው የሶቪየቶች መሪ ኒኪታ ኩርቺየቭ ቀጭን ትዕዛዝ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት በአንድ ሌሊት ምስራቅ በርሊን ዙሪያዋን በ155 ኪሎ ሜትር መጠነ ዙሪያ የማገጃ አጥር ተገጠገጠባት፡፡

የድንበር ጠባቂ ፖሊሶችም የተኩሰህ ግደል ፈቃድ ተሰጣቸው፡፡ በዘመኑ ግንቡን ዘለው ወደ ምዕራብ በርሊን ለመሻገር የሞከሩ ብዙዎች የአልሞ ተኳሾች ጥይት ዒላማ ሆነዋል፡፡

በዚህ አይነቱ ሙከራ የተገደሉት ከ200 እንደማያንሱ ይነገራል፡፡
                                               

በጊዜ ሂደት የሽቦ አጥሩ ከፍታ ጨምሮ ወደ ኮንክሪት ግንብነት ተለወጠ፡፡

ጊዜ አለፈ፡፡ 
ታሪክ እየተለወጠ መጣ፡፡

የቀድሞዋን ሶቪየት ኅብረት ጨምሮ በምስራቅና መካከለኛው አውሮፓ አገሮች የለውጥ ንፋስ መንፈስ ጀመረ፡፡

ያ የለውጥ ነፋስ ወደ ምስራቅ ጀርመንም ነፈሰ፡፡ 
ሕዝቡ እምቢ ለመብቴ ብሎ ተነሳ፡፡

አገዛዙ እንደ በፊቱ ሊያቆመው ሊቆጣጠረውና ሊያስታግሰው አልቻለም፡፡ 
የምስራቅ ጀርመን ሹሞች ሳይወዱ በግዳቸው የግንቡ ማገጃነት እንዲያበቃ ወሰኑ፡፡ 

ያሻው ሁሉ ወደ ምዕራብ በርሊን መሻገር ይችላል አሉ፡፡

አዋጁ እንደተሠማ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ምስራቅ ጀርመናውያን ወደ ምዕራብ በርሊን ለመሻገር ወደዛው ተመሙ፡፡ የግንቡ መውጫ በሮች እንዲከፈቱላቸው ጠየቁ፡፡

አዋጁን ያላጣጣሙትና ግራ የተጋቡት የድንበር ጠባቂ ፖሊሶች አለቆቻቸውን ማብራሪያ መጠየቁን ተያያዙት፡፡ ግንቡን ክፍት አድርጉት ተባሉ፡፡ ሕዝቡ ጐርፍ ሆኖ ወደ ምዕራብ በርሊን ተመመ፡፡ ይሄ ከሆነ ዛሬ 28ኛ ዓመቱ ሆነ፡፡ የበርሊን ግምብ መውደቅ እንደ አገሪቱ ዳግም ውህደት ቀዳሚ ምልክት ተቆጠረ፡፡

ከጥቂት ዓመታት በኋላ የተነጣጠለችዋ ጀርመን ዳግም ተዋሐደች፡፡ 
የበርሊን ግምብ ፍርስራሽ ቅሪት የቀዝቃዛው ጦርነት ማክተም ተምሳሌታዊ ምልክት ተደርጐ ይታያል፡፡

ምንጭ:- የሸገር FM 102.1 ሬዲዮ

Advertisement