የዩኒቨርሲቲ ዕጩ ምሩቃን የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ሊወስዱ ነው – University Graduates Are Going to Take a Qualification Exam.

                                                    

ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ በአገሪቱ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን አጠናቀው ለመመረቅ ዝግጁ የሆኑ ተማሪዎች፣ የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ሊወስዱ መሆኑ ታወቀ፡፡

ሰሞኑን በትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፣ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ በሁሉም የቅድመ ምረቃ ትምህርት መስኮች ተማሪዎች ከመመረቃቸው በፊት የብቃት መለኪያ የሚሆነውን አጠቃላይ ምዘና ወስደው አጥጋቢና ከዚያ በላይ ውጤት ማስመዝገብ ይኖርባቸዋል፡፡ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ አጠቃላይ ምዘና መስጠት የምሩቃንን ዕውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት ለመመዘን የላቀ ሚና እንደሚጫወት በደብዳቤው ተገልጿል፡፡

 በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ከሴሚስተር ሴሚስተር የሚያሸጋግራቸው ውጤት ካገኙ በቀጥታ ተመርቀው ይወጡ እንደነበር ይታወሳል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውን አጠናቀው ለመመረቅ ዝግጁ ሲሆኑ፣ የብቃት ማረጋገጫ ፈተና መስጠት አዲስ ጉዳይ ሆኖ እያነጋገረ ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ሪፖርተር ተማሪዎችን ያነጋገረ ቢሆንም፣ ምንም መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ጉዳዩ እውነት ከሆነ በጣም የሚያሳዝንና ለመቀበልም ከባድ ነው ያሉ አሉ፡፡

ለ36 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የተጻፈው ደብዳቤ እንደሚገልጸው፣ ለተማሪዎች የመውጫ ፈተና መስጠት አገሪቱ ከምትፈልገው የተማረ የሰው ኃይል ጋር ለማዛመድ ነው፡፡ የመውጫ ፈተናውን ማለፍ የማይችሉ ተማሪዎች ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን በደብዳቤው አልተገለጸም፡፡

ምንጭ:- ሪፖርተር

Advertisement