ሄግ ፍርድ ቤት የቀረበው የቀይ ሽብር ተከሳሽ ምስክሮችን እንዲያድኑት ተማፀነ – Red Terror Trial

                                                      

ኢትዮጵያ ውስጥ ከ40 ዓመት በፊት በተፈፀመው ”ቀይ ሽብር” ወቅት ተሳታፊ ነበር ተብሎ ኔዘርላንድስ ውስጥ በጦር ወንጀል የተከሰሰው ግለሰብ የድርጊቱ ሰለባዎች ከክሱ ነፃ እንዲያወጡት ተማፀነ።

ኢትዮጵያን ለ17 ዓመታት የመራው እጅግ የሚፈራው ወታደራዊ ቡድን ደርግ አባል እንደነበረ ያመነው እሸቱ አለሙ፤ በፍርድ ቤቱ ውስጥ ከኋላው ተቀምጠው ወደነበሩት የቀይ ሽብር ሰለባዎች በመዞሮ ”እባካችሁ ከዚህ ነገር አድኑኝ። አዎ ድርጊቱ ተከስቷል፤ ቢሆንም ግን እኔ የለሁበትም። በቦታው አልነበርኩም” ሲል ተማፅኗቸዋል።

“ወንጀለኛ አይደለሁም። ከዚህ በኋላ መኖርም አልፈለግም” ሲልም ለሄግ ዳኞች ተናግሯል እሸቱ።

ትናንት በነበረው የፍርድ ቤት ውሎ አምስት ሰዎች ዘመዶቻቸውን ማጣታቸውን ለችሎቱ ተናግረዋል።

ከእነዚህም መካከል አንዲት ሴት “በጣም ውብና ቅን ወንድሜ የት እንደገባ ሳላውቀ አጥቼዋለሁ” ስትል ምስክርነቷን ሰጥታለች።

የሴትየዋ ጠበቃ ሁለት ያረጁ ፎቶዎችን በምስክረነት ለዳኞች አስረክቧል።

እጅግ በሃዘን እንደተጎዳች የገለፀችው ምስክር “በስተመጨረሻም ፍርድ ሲሰጥ ለማየት በመብቃቴ ዕድለኛ ነኝ” ስትል ተደምጣለች።

ሌላ የድርጊቱ ሰለባ ”በጨለማ ክፍል” ውስጥ እንደታሰሩ እማኝነታቸውን ሰጥተው፤ 82 ሰዎች ሲገደሉ ማየታቸውን እና አስከሬናቸውም በአንድ የጅምላ መቃብር እንደተቀበረ ተናግረዋል።

በቀጣይ ቀንም አሳሪዎቹ የተገደሉትን ሰዎች የጋብቻ ቀለበትና ልብሶቻቸውን ለብሰው እንዳዩ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

እሸቱ አለሙ በቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ተገደሉ በተባሉ 75 ሰዎች፣ ሰቆቃ በመፈፀም፣ በጅምላ እስር እና ከህግ ውጪ ሰዎችን በማሰርን የቀረቡበትን አራት የጦር ወንጀሎችን አልፈፀምኩም ብሏል።

የፍርድ ሂደቱ በሦስት ሳምንታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement