ሳይፖቭ ብዙ ሰዎችን ለመግደል እቅድ ነበረው

                                             

ኒው ዮርክ ላይ መኪናን በመጠቀም ስምንት ሰዎች ለሞቱበት ጥቃት ዋነኛ ተጠርጣሪ የሆነው ግለሰብ የቻለውን ያህል በርካታ ሰዎችን ለመግደል አስቦ እነደነበር ተናገረ።

የ29 ዓመቱ ሰይፉሎ ሳይፖቭ ለመርማሪዎች እንደተናገረው ዓመት ያህል አቅዶ ስለፈፀመው ጥቃት ”ደስተኛ ነኝ” ብሏል።

ጥቃት በፈፀመበት ስፍራ በፖሊስ ቆስሎ የተያዘው የኡዝቤክስታኑ ስደተኛ ከፌደራል መንግሥቱ የሽብር ክስ የሚጠብቀው ሲሆን፤ አይኤስ በሚፈፅማቸው ጥቃቶች መነቃቃቱን ይናጋራል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በቲዉተር ላይ ባሰፈሩት ፅሁፍ እንዳመለከቱት የሞት ቅጣት ይጠብቀዋል ብለዋል።

ተጠርጣሪው ምን አለ?

ማክሰኞ ማንሃተን ውስጥ እግረኞችንና ብስክሌት የሚጋልቡ ሰዎችን በመኪና እየገጨ የገደለው ሳይፖቭ ከጥቃቱ 24 ሰዓታት በኋላ በተሽከርካሪ ወንበር እየተገፋ ፍርድ ቤት ቀርቧል።

ስድስት ሰዎች በጥቃቱ ስፍራ ህይወታቸው ሲያልፍ ሁለቱ ደግሞ ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ ነበር የሞቱት። በተጨማሪም 12 ሰዎች ሲቆስሉ ከመካከላቸው አራቱ በአስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።

የአቃቢ-ህግ ባልደረቦች እንዳሉት ሳይፖቭ በእስር ቤት እያለ እራሱን ጥፋተኛ ለሚያደርጉ ንግግሮቹ ግድ ሳይኖረው ዘና ብሎ ነበር ቃሉን የሰጠው።

የፌደራል ፍርድ ቤት ሰነዶች እንደሚያመለክቱት፡

  • ጥቃቱን ከሁለት ወራት በፊት ማቀዱንና ባለፈው ወር መኪና ተከራይቶ አካባቢውን መቃኘቱን
  • በርካታ ሰዎች በመንገድ ላይ ይኖራሉ በማለት አስቦበት የሃሎዊን እለትን እንደመረጠ
  • በመጀመሪያው እቅዱ ብሩክሊን ድልድይ ላይም ጥቃት ለመፈፀም አስቦ እንደነበር
  • በጥቃቱ ጊዜ በመኪናው ላይ የአይኤስን ባንዲራ ለመስቀል አስቦ የነበረ ቢሆንም ትኩረት ላለመሳብ እንደተወው
  • ጥቃቱን ለመፈፀም 90 የሚደርሱ ሞባይል ስልኩ ላይ በተገኙ አሰቃቂ ቪዲዮዎች እንደተነቃቃ፤ በተለይ ደግሞ የአይ ኤሱ መሪ አቡባከር አልባግዳዲ ኢራቅ ውስጥ የሚያጋጥመውን ሞት ሙስሊሞች እንዴት መበቀል እንዳለባቸው ያቀረበው ጥሪ እንደሆነ ተናግሯል።

ሳይፖቭ አንድ ክስ ለአይኤስ የተለያዩ ድጋፎችን በመስጠት ሌላ ክስ ደግሞ ተሽከርካሪዎች ላይ ውድመትን በማድረስ ቀርቦበታል።

የኒው ዮርክ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር የሆኑት ጆን ሚለር ተጠርጣሪው ተመሳሳይ ጥቃቶችን ለመፈፀም አይ ኤስ የሚከተለውን መመሪያ በትክክል ተግባራዊ አድርጓል።

የሃገር ውስጥ ደህንነት ተቋሙ ኤፍቢአይ የ32 ዓመትቱ ኡዝቤክስታናዊ ሙሃማድዞይር ካዲሮቭ የተባለ ግለሰብ ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ ለጥያቄ እንደያዘው ገልጿል።

 

ምንጭ: ቢቢሲ

 

Advertisement