ኳታር ለሠራተኞቿ ዝቅተኛውን የደሞዝ ክፍያ ገደብ አስቀመጠች – Qatar Sets Minimum Wage For Its Guest Workers

 

ኳታር የተለያዩ ሠራተኞችን የሚመለከቱ ሕጎች በማርቀቅ እና በማሻሻል ላይ ትገኛለች። ከእነዚህ መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ ያፀደቀችው የዝቅተኛ ደሞዝ ክፍያ ገደብ አንዱ ነው።

ከ2022 የዓለም ዋንጫ ዝግጅት ጋር ተያይዞ በኳታር ታሪክ በቁጥሩ ከፍተኛ ነው የተባለ ሠራተኛ ዶሃ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ሥራ ላይ ይገኛል። ይህንን ተከትሎም ዓለም አቀፍ የሠራተኞች መብት ተከራካሪ ድርጅቶች የኳታር ሠራተኛ አያያዝ ላይ ጥያቄ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት (አይኤልኦ) ኳታር ወርሃ ሕዳር ከማብቃቱ በፊት ባላት የሠራተኛ ሕግ ላይ ክለሳ ካላደረገች የከፋ ነገር ይከተላል ብሎ ካስጠነቀቀ በኋላ ነው ሃገሪቱ ማሻሻያ ያደረግችው።

የዓለም አቀፉ የሠራተኞች ሕብረት ኮንፈደሬሽን ዋና ፀሓፊ የሆኑት ሻሮን ባሮው ለውጡ በኳታር ለዘመናዊ ባርነት ማክተም ምልክት ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

ኳታር ለረጅም ጊዜ ‘ካፋላ’ የተባለ ቀጣሪ ድርጅቶች ካልፈቀዱ በስተቀር ከውጭ ሃገር የሚመጡ ሠራተኞች ድርጅቱን ለቀው ወደሌላ ቀጣሪ ድርጅት ወይም ሃገሪቱን ለቀው መሄድ እንዳይችሉ የሚያደርግ አሠራር ስትከተል ቆይታለች።

ኳታር ከታህሳስ 2016 ጀምሮ ካፋላ የተባለው አሰራር ተግባራዊ እንዳይሆን ማድረጓ ይታወሳል። 

 

በአዲሱ ማሻሻያ አብይ ለውጥ ያመጣሉ የተባሉ የሠራተኛ ሕግጋትን ያዘለ እንደሆነ ታውቋል። ከእነዚህም መካከል

• ፆታ ሳይለይ ለሠራተኞች የሚከፈል ዝቅተኛ የደሞዝ መጠን ገደብ እንዲኖረው

• ከወጭ ሃገር የሚመጡ ሠራተኞች ሃገሪቱን ለመልቀቅ የቀጣሪዎቻቸውን ፈቃድ መጠይቅ እንዳይሹ

• መታወቂያ ካርዶች በቀጣሪ ድርጅቶች ሳይሆን በመንግሥት እንዲሰጥ እና መሰል ሕግጋትን ያዘለ ነው።

የኮንፈደሬሽኑ ዋና ፀሓፊ ባሮው እንደሚሉት አሁንም ብዙ የሚቀሩ ጉዳዮች ቢኖሩም እርምጃው አውንታዊ የሚባል ነው።

አዳዲሶች ማሻሻያዎች መቼ ሥራ ላይ መዋል እንደሚጀምሩ ግን አስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

ከ1.5 እስከ 2 ሚሊዮን የሚደርሱ እና በአብዛኛው ከእስያ እንደመጡ የሚነገርላቸው የጉልበት ሠራተኞች በኳታር የግንባታ ዘርፍ ተሰማርተው እንደሚገኙ ይገመታል።

በ2013 የዓለም አቀፉ የሠራተኞች ሕብረት ኮንፈደሬሽን ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው 1200 ያህል ከውጭ ሃገራት የመጡ ሠራተኞች በ2022 ዓለም ዋንጫ ዝግጅት በሚካሄዱ ግንባታዎች ላይ ተሰማርተው ሳለ ሕይወታቸው አልፏል።

ምንጭ: ቢቢሲ 

 

 

Advertisement