ታይፎይድን የመከላከል አቅሙ ከፍተኛ ነው የተባለ ክትባት ጥቅም ላይ ሊውል ነው – A New Typhoid Fever Vaccine Has Been Recommended

                                               

የመከላከል አቅሙ ከፍተኛ ነው የተባለው አዲስ የታይፎይድ መከላከያ ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል የዓለም ጤና ድርጅት አዟል።

አዲሱ የታይፎይድ ክትባት ከ10 የታይፎይድ ህመሞች እስከ ዘጠኝ የሚደርሱትን ሙሉ በሙሉ መከላከል ይችላል ነው የተባለው።

የጤና ዘርፍ ተመራማሪዎች እንደሚናገሩት፥ በየዓመቱ 22 ሚሊየን ሰዎች በታይፎይድ ይጠቃሉ፤ ከዚህም ወስጥ 220 ሺህ ሰዎች ደግሞ በዚህ በሽታ ምክንያት ህይወታቸውን ያጣሉ።

ታዲያ አዲሱ የታይፎይድ ክትባት በዚህ ደረጃ በሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንሰው ተስፋ እንደተጣለበትም ተናግረዋል።

ክትባቱ በተለይም በታይፎይድ በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቁት ህጻናትን ከበሽታው እንደሚታደግም ተነግሮለታል።

እንዲሁም ሀገራት ታይፎይድ በሽታን እንዲያስወግዱ ይረዳቸዋልም ተብሏል።

“ታይፊ” በሚባል ባክቴሪያ አማካኝነት የሚከሰተው የታይፎይድ ምልክቶች፦

  • ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ትኩሳት
  • ከፍተኛ የራስ ምታት
  • ማቅለሽለሽ
  • የምግብ ፍላጎት መቀነስ
  • የሆድ ድርቀት ናቸው።

የታይፎየድ አምጪ “ታይፊ ባክቴሪያ” በተበከለ ምግብ እና ውሃ አማካኝነት ነው የሚሰራጨው።

በሽታው በብዛት ንጹ የመጠጥ ውሃ እጥረት እና የንፅህና ችግር በሚስተዋልባቸው ደሃ ገሮች ይስተዋላል የተባለ ሲሆን፥ ደቡብ እሲያ እና ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ በሽታው በብዛት እንደሚስተዋልም ተነግሯል።

በአሁኑ ጊዜ ሁለት የታይፎይድ ክትባቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ፈቃድ የተሰጣቸው ሲሆን፥ እስካሁን ግን እድሜያቸው ከ2 ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት ለሚሰጥ ክትባት እስካሁን ፈቃድ አልተሰጠም።

ከዚህ በኋላ ግን ለህፃናት በአንድ መርፌ ብቻ በሽታውን ለመከላከል የሚያስችል ክትባት እንደሚሰጥ ተነግሯል።

አዲሱ ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ጥቆማ የሰጡት የዓለም ጤና ድርጅት የአማካሪዎች ቡድን መሆኑም ተነግሯል።

የአማካሪዎቹ ቡድን ሊቀመንበር ፕሮፌሰር አሌሀንድሮ ከራቪቶ፥ ታይፎይድን በመከላከሉ ረገድ ለመጀመሪያ ጊዜ ውጤታማ የሆነ ክትባት እንደተገኘ እምነት አለኝ ብለዋል።
ቡድኑ፥ ከ6 ወር እድሜ ጀምሮ ያሉ ህፃናት ክትባቱን ቢወስዱ መልካም ነው ሲልም ምክሩን ለግሷል።

በታይፎይድ በሽታ ከተጠቁ 5 ሰዎች ውስጥ አንዱ ህይወቱ እንደሚያልፍ መረጃዎች የሚያመለክቱ ሲሆን፥ አሁን ባለው ተጨማጭ ሁኔታ ይህ አሃዝ በከፍተኛ ደረጃ ጭማሪ እያሳየ ነው።

አዲሱ የታይፎይድ ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል መደረጉ በየዓመቱ በዚህ በሽታ አማካኝነት የሚከሰቱ ሞቶችን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ተነግሯል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement