NEWS: የፌደራል መንግስት ግጭት በተቀሰቀሰባቸው የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች ነፃ ቀጠና አቋቁሞ ለማረጋጋት እየሰራ መሆኑን ገለፀ

                                               

የፌደራል መንግስት ግጭት በተቀሰቀሰባቸው የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ከግጭት ነፃ ቀጠና አቋቁሞ ለማረጋጋት እየሰራ መሆኑን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ገለፁ።

ሚኒስትሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በክልሎቹ አንዳንድ አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት በመቀስቀስ እና ጉዳት በማድረስ ተጠያቂ የሆኑ አካላትን መንግስት በቁጥጥር ስር የማዋሉን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በግጭቱ ሳቢያ ለተፈናቀሉ ዜጎች ጊዜያዊ ድጋፎች እየተደረጉ ሲሆን፥ ዜጎች ለዘለቄታው ራሳቸውን ስለሚችሉበት ሁኔታ መንግስት በየደረጃው ከህዝብ ጋር እየመከረ ነው ብለዋል፡፡

በግጭቱ ህይወት መጥፋቱን፣ የአካል ጉዳት መድረሱን እና ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ወጥተው በጊዜያዊ መጠለያዎች እየኖሩ መሆኑን ዶክተር ነገሪ ተናግረዋል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራ ሀገር አቀፍ ግብረ ሃይል በዜጎች ላይ የደረሰውን ጉዳት፣ በድሬዳዋ፣ ሀረር ከተማ አማሬሳና በባቢሌ የሚገኙ መጠለያዎችን መጎብኘቱን እና በግጭቱ ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸውን አካላት ማነጋገሩን ነው ሚኒስትሩ የጠቀሱት።

ከተፈናቃዮች ጋር በተደረገ ውይይትም ጉዳቱን ያደረሱት የፀጥታ ሃይሎች እንጅ ህዝቦች እንዳልሆኑ፣ የከፋ ጉዳት እንዳይደርሰባቸው በማድረግ በኩል የሀገር መከላከያ ሰራዊት ትልቅ እገዛ ማድረጉን፣ በግጭት ወቅት የሁለቱም ክልሎች ህዝቦች አንዱን ከሌላው ጥቃት በመከላከል መስዋዕትነት መክፈላቸውን መናገራቸውን ነው ያስታወሱት።

የልኡካን ቡድኑ በዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰ ያረጋገጠ ሲሆን፥ ለተጎጅዎች እየተደረገላቸው የሚገኘውን ድጋፍ መገምገሙን በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።

ግብረሃይሉ ችግሮች በጊዜያዊነትና በዘለቄታ የሚፈቱበትን አቅጣጫ ማስቀመጡን ጠቁመው፥ በአሁኑ ወቅት በሁለቱም ክልሎች የስጋት ቀጠናዎች አካባቢ የታጠቁ ሃይሎች እንዳይደርሱ መደረጉን ገልጸዋል።

ዶክተር ነገሪ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ሪፖርትን ዋቢ አድርገው እንደገለጹት፥ በኦሮሚያ ክልል አወዳይ ከተማና አካባቢ በቀጥታ በግጭቱ ላይ በሰብዓዊ መብት ጥሰት እና በግድያ ወንጀል የተሳተፉ አጥፊዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ ነው ብለዋል፡፡

በአንፃሩ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በተመሳሳይ መልኩ በወንጀል ድርጊት የተሳተፉ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ለማዋል በክልሉ በኩል የተወሰደ ያለው እርምጃ አጥጋቢ እንዳልሆነ አንስተዋል።

ለዚህም የፌደራል ፖሊስ አስፈላጊውን መረጃ እያደረጀ ተጠርጣዎቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚስራው ስራ ተጠናክሮ እንደቀጠለና የክልሉ አመራሮችም ሀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው የፌደራል ፖሊስ ማሳሰቡን ተናግረዋል፡፡

አካባቢው የወጪ ገቢ ንግዶች መተላለፊያ ኮሪደር እንደመሆኑ መጠን በመንገዶች ላይ ገና ያልተፈቱ ችግሮች እንዳሉና የወጭ ገቢ ምርቶች ላይ መስተጓጎሎች መኖራቸውን ነው ያነሱት።

ችግሩን ለመፍታት የንግድ ሚኒስቴር እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሁለቱ ክልሎች አካላት እየተነጋገሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ጫትና ሌሎች የወጪ ምርቶችን በማምረትና በመሸጥ በሚተዳደሩ አርሶ አደሮችና ላኪዎች ላይ ኢኮኖሚያ ኪሰራ መድረሱን፥ ሀገሪቱ ከዘርፉ በምታገኘው የውጭ ምንዛሬ ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ዶክተር ነገሪ አመላክተዋል፡፡

እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ በዚህ ጉዳይ ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ኦቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት የፌደራል ፖሊስና የመከለከያ ሰራዊት በኮሪደሩ አካባቢዎች የዜጎችን ህገ መንግስታዊ መብትና የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡

ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት አማራጮች እንዳሉ ሆነው ከዚህ ያለፈ መጉላላት፣ ሁከትና ግርግር የሚፈጥሩ አካለት ላይ መንግስት ከመቼው የበለጠ ክትትል እና እርምጃ እንደሚወስድ አሳስበዋል፡፡

ለተፈናቃዮች አስፈላጊው የእለት ደራሽ እርዳታ በፌደራል የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽንና በሁለቱም ክልሎች በኩል እየቀረበላቸው መሆኑ በመግለጫው ተጠቅሷል።

በመግለጫው እንደተጠቀሰው ለህፃናትና እናቶች አልሚ ምግብ እየቀረበላቸው ሲሆን፥ የፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና ክልሎች በጋራ የህክምና ባለሙያዎችን የያዘ ሰባት የህክምና ቡድን 24 ሰዓት የጤና ክትትል እያደረገ ነው።

ከትምህርት ገበታቸው የተፈናቀሉ ህጻናት ወደ ቀያቸው እስኪመለሱ ድረስ ጊዜያዊ የትምህርት አማራጭ የሚያገኙበት እድል እንዲመቻችላቸው አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

አንዳንድ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው ክልል ሄደው ለመማር ስጋት እንዳለባቸው መግለፃቸውን ያነሱት ዶክተር ነገሪ፥ ተማሪዎች ትምህርታቸውን መከታተል እንደሚችሉና ምንም ችግር እንደማይደርስባቸው መንግስት ከትምህርት ተቋማት ጋር እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አዲስ ተመዳቢ ተማሪዎች ገና ያልተጠሩ እና ወደ ዩኒቨርሰቲዎች ያልገቡ ቢሆንም፥ ነባር ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆኑን ሚንስትሩ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል፡፡

በሁለቱ ክልልች ለሚኖሩ ህዝቦች የሚሰራጩ መረጃዎች በአንድም ሆነ በሌላ መልክ ግጭቱን የሚያባብሱ መሆን እንደሌለባቸው፥ ይልቁንም ግጭቱን ለዘለቄታው በመፍታት ላይ ያተኮሩ፣ የሀገራችንን ሰላም የሚያስጠብቁ እና የህዝቦቻችንን የአብሮነት እሴቶች የሚያጎለብቱ ሊሆኑ ይገባቸዋል ነው ያሉት በመግለጫቸው።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement