በኢትዮጵያ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ወረርሽኝ ሊባል በሚችል ደረጃ እየተስፋፋ መምጣቱ ተገለፀ

                                                       

በትዕግስት አብርሀም

በኢትዮጵያ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ወረርሽኝ ሊባል በሚችል ደረጃ እየተስፋፋ መምጣቱ ተገለፀ።

በዓመት ከ27 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ይይዛሉ የተባለ ሲሆን፥ ከ19 ሺህ በላይ የሰዎች ደግሞ በቫይረሱ አማካኝነት ይሞታሉ ነው የተባለው።

በዚህ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ውይይት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና በፌዴራል የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ፅህፈት ቤት አዘጋጅነት በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ እንደተገለፀው ይበልጥ ተጋላጭ በሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የስርጭት ምጣኔው ከ2 ነጥብ 5 እስከ 25 በመቶ ደርሷል።

በትልልቅ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክቶች፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ የአበባ ልማትና መሰል ሰፋፊ የልማት አካባቢዎች የኤች አይ ቪ አጋላጭ ባህሪያት መስፋት ለቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ ስጋት ሆኗል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ከበደ ወርቁ፥ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረት የተመዘገበው ለውጥ መዘናጋት መፍጠሩን አንስተዋል።

ከአምስት እና ስድስት ዓመት በፊት የነበረውን ኤች አይ ቪን የመግታት ስራ ለመድገም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሀላፊነታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

Advertisement