አይቴል በኢትዮጵያ የገጣጠማቸውን ስልኮች ወደ ውጭ በመላክ 40 ሚሊየን ዶላር ለማግኘት አቅዷል

                                                        

የአይቴል ሞባይል በኢትዮጵያ የገጣጠማቸውን የሞባይል ስልኮች ለውጭ ገበያ በማቅረብ በተያዘው ዓመት 40 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት ማቀዱን ገልጿል።

ኩባንያው በ10 ዓመት ውስጥ የተለያዩ የሞባይል ስልክ ዓይነቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከ35 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግሯል።

በተጨማሪም እስከ ሁለተኛው የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መጨረሻ ድረስ 300 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ለማስገባት እየሰራ መሆኑን ነው የጠቆመው።

እቅዱን ለማሳካት የሚያስችለውን ፋብሪካ በአይ.ሲ.ቲ. ፓርክ ለመገንባት ስምምነት ላይ መደረሱን የኩባንያው ምክትል ማናጀር አቶ ቢኒያም አረዓያ ተናግረዋል።

አቶ ቢኒያም፥ እስካሁን ከ20 በላይ የሚሆኑት አዳዲስ ሞዴሎችን ለሀገር ውስጥ እና ውጭ ገበያ በማቅረብ ውጤታማ ስራ መሰራቱን ነው የጠቀሱት።

በቀጣይ አዳዲስ ሞዴል ስማርት ስልኮችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ገቢውን እና የድርጅቱን የማምረት አቅም ለማሳደግ እንደሚሰራ ተነግሯል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement