NEWS: የሳምሰንግ ኤሌክትሮኒክስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ባልተጠበቀ ሁኔታ ሃላፊነታቸውን ለቀቁ

                                                 

የሳምሰንግ ኤሌክትሮኒክስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ክዎን ኦህ-ህዩን ባልተጠበቀ ሁኔታ ሃላፊነታቸውን ለቀቁ።

ሳምሰንግ የቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያ ሊቀመንበሩ ባሳለፍነው ነሃሴ ወር በሙስና ወንጀል ወደ ማረሚያ ቤት ከወረዱ ወዲህ አስተዳደራዊ አለመረጋጋት ላይ ነው።

አሁን ሃላፊነታቸውን የለቀቁት፥ ሚስተር ክዎን ከሶስቱ የሳምሰንግ ኤሌክትሮኒክስ ዋና ስራ አስፈጻሚዎች አንዱ ናቸው።

ኩባንያው የሩብ ዓመት ከፍተኛ የሽያጭ ገቢ እንደሚያገኝ በሚጠበቅበት ጊዜ ሃላፊነታቸውን መልቀቃቸውም አነጋጋሪ ሆኗል።

በሳምሰንግ ኤሌክትሮኒክስ ቦርድ ውስጥ ያገለገሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው፥ ከዚህ ቀደም ስራውን ለመልቀቀቅ ይፈልጉ እንደነበር ጠቅሰዋል።

“ኩባንያው ባልተጠበቀ የአስተዳደር ቀውስ ውስጥ በመሆኑ በአዲስ መንፈስ እና ወጣት አመራር ታግዞ በየጊዜው እየተለዋወጠ ለሚመጣው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፈተና ብቁ ምላሽ እንዲሰጥ ስራየን ለቅቂያለሁ” ብለዋል።

እስክ መጪው የፈረንጆቹ 2018 መጋቢት ወር ድረስም በሳምሰንግ ኤሌክትሮኒክስ ቦርድ አባልነታቸው እንደሚቆዩ ነው የጠቆሙት።

የሳምሰንግ ኩባንያ ቃል አቀባይ ስለሁኔታው ተጠይቀው፥ ምክትሎች በዋና ስራ አስፈፃሚነት ቦታው ላይ እንደሚሾሙ ተናግረዋል።

ሳምሰንግ ግሩፕ 60 እህት ኩባንያዎችን አካቶ የተዋቀረ ግዙፍ ድርጅት ሲሆን፥ የደቡብ ኮሪያ መንግስት በሙስና ወንጀል ተሳታፊነት ብዙ ጊዜ ወንጅሎታል።

በዚህም ባለፈው ነሃሴ ወር የኩባንያው ሊቀመንበር፥ ሊ ጄ ያንግ ጉቦ እና ሌሎች የሙስና ወንጀሎችን ፈፅመዋል በሚል አምስት ዓመት እስር ተፈርዶባቸዋል።

ሚስተር ሊ ለቀድሞዋ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት ፓርክ ጊዩን ሄይ ጓደኛ እና አብሮ አደግ ቾይ ሱን ሲል፥ የበጎ አድራጎት ድርጅት 41 ቢሊየን ዎን ወይም 36 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ሰጥተዋል በሚል መከሰሳቸው ይታወቃል።

ሰውየው ይህን ያደረጉት ከፕሬዚዳንት ጊዩን ሄይ ፖለቲካዊ ጥቅም ለማግኘት ነው በሚል ተወንጅለው ፍርድ ተላልፎባቸዋል።

ትናንት የእስር ውሳኔው አይገባኝም የሚል ይግባኝ ለመጠየቅ ፍርድ ቤት መታየታቸው ነው የተነገረው።

በሳምሰንግ ኩባንያ ያንዣበበው የአመራር ችግር የኩባንያውን መሰረት ያናጋዋል ተብሎ ባይታሰብም፥ ስጋቱ ግን ከፍተኛ ነው ይላሉ በቅርበት የሚከታተሉ ተንታኞች።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement