NEWS: በትግራይ ክልል የተገኘው የሳፋየር ማዕድን በዓለም ገበያ የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝ እየተሰራ ነው

                                                  

በፋሲካው ታደሰ

 በትግራይ ክልል የተገኘው የሳፋየር ማዕድን በዓለም ገበያ የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝ “የኢትዮጵያ ሳፋየር” ተብሎ የምስክር ወረቀት እንዲያገኝ እየሰራ መሆኑን የትግራይ ክልል የማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ሳፋየር በአለም ላይ በከበሩ ማዕድናት ዘርፍ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ማዕድናት መካከል አንዱ ነው።

ውብ ሰማያዊ፣ ውስጡ ብርሃን የሚያስተላለፍ እና ጥሩ መጠን ይዞ የሚገኝ ሳፋየር የሚገኝባቸው የዓለም ክፍሎች ጥቂት ናቸው።

ሀምራዊ፣ ቢጫ እና አረንጓዴ ቀለም ያለው ሳፋየር ደግሞ እንደየቅደም ተከተላቸው ዋጋቸው እያነሰ ይሄዳል።

የተለያየ ቀለማትን በአንድ ያጠመሩ ሳፋየሮች እንደሚገኙም መረጃዎች ያሳያሉ።

በኢትዮጵያ ከአስር ዓመት በፊት በደቡብ ክልል የተገኘው ማእድኑ በቅርቡም በትግራይ ክልል በመካከለኛው፣ ሰሜን፣ ምዕራባዊ እና ምስራቃዊ ዞኖች ተገኝቷል።

የከበረ ማዕድኑ በክልሉ የዳሰሳ ፍቃድ በተሰጣቸው ባለሃብቶች አማካኝነት ተገኝቶ ሳፋየር መሆኑ በኢትዮጵያ ጂዮሎጂካል ሰርቬይ ተረጋግጧል።

ሳፋየር በአብዛኛው ለጌጣጌጦች መስሪያነት የሚውል የከበረ ማዕድን ነው፤ በጣም ጠንካራ በመሆኑም የተለያዩ እቃዎችን ለመቁረጥ እና ለመሞረድም ሊያገለግል ይችላል።

በአለም አቀፍ ደረጃም ተፈላጊነቱ ከፍ ያለ በመሆኑ 1 ግራም ማለትም 5 ካራት አንደኛ ደረጃ ሳፋየር ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያወጣ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ይናገራሉ።

የትግራይ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ስራ አስኪያጅ አቶ መዓርግ ሓዱሽ፥ በክልሉ በተለያዩ ወረዳዎች የሳፋየር ማዕድን መገኘቱ ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

ሳፋየር የተገኘባቸውን ቦታዎች የመከለሉ ስራም ቀዳሚው መሆኑን ያነሳሉ።

ኤጀንሲው ከብሪታኒያ ጂሞሎጂስት ሶሳይቲ ጋር በመሆን ባለሙያዎች ተልከው ሳፋየረ የተገኘባቸው አካባቢዎች ቅኝት እንዲደረግባቸው አድርጓል።

ባለሙያዎቹ አምራቾችን በማግኘት የገበያውን ሁኔታ ያጠኑ ሲሆን፥ የማዕድኑ ጥራትን የማረጋገጥ ስራም ተከናውኗል ብለዋል አቶ መዓርግ ።

ይህም በቅርቡ በሚወጣው የብሪታኒያ ጂሞሊጂስት ሶሳይቲ ጆርናል ላይ ታትሞ እንደሚወጣ ገልፀዋል።

የከበረ ማዕድኑ በአለም ገበያ የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝ ከማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ፈቃድ የወሰዱ 30 ላኪዎች በገበያ ማዕከላት ገብተው ግብይት እንዲፈጽሙ እየተደረገ ነው።

ላኪዎቹ ከአምራቾቹ ከገዙት 24 ኪሎ ግራም ማዕድን ወደ ወጭ ለመላክ ተሞክሮም ማዕደኑ አንደኛ ደረጃ ያለው መሆኑ ተረጋግጧል ነው ያሉት አቶ መዓርግ ።

ወደ ውጭ የተላከው ሳፋየር በማስታወቂያ ዋጋ ለገበያ በመቅረቡም በሀገር ውስጥ ካለው ዋጋ ቀንሶ 1 ኪሎ ግራሙ በ10 ሺህ የአሜሪካ ዶላር መሸጡን ጠቅሰዋል።

ባለፉት ወራት ማዕድኑ በማስተዋቂያ ዋጋ ለውጭ ገበያ ቀርቦም ከ240 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱ ተመልክቷል።

ይህም ከአለም አቀፉም ሆነ ከሀገር ውስጥ ዋጋ ጋር ሲነፃፀር በጣም አነስተኛ መሆኑን ነው ስራ አስኪያጁ የሚናገሩት።

ከማዕድኑ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ለአለም ገበያ በሚቀርበው ሳፋየር ላይ የዋጋ ክለሳ የተደረገ ሲሆን፥ የ1 ኪሎ ግራሙ ዋጋ ወደ 35 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ከፍ እንዲል ተወስኗል። ይሁን እንጂ ይህም ከአለም ገበያ ጋር ሲወዳደር አሁንም በጣም ዝቅተኛ ነው።

በክልሉ ወጣቶች ፈቃድ አውጥተው በመደራጀት በዘርፉ እንዲሰማሩ እየተደረገ መሆኑን አቶ መዓርግ ገልፀዋል።

ሳፋየር በማምረት ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ለአንድ አመት ከሰሩ በኋላ በሌሎች ወጣቶቸ እንዲተኩ ይደረጋል።

አቶ መዓርግ የሳፋየር ማዕድኑን በማውጣት ወጣቶች በስፋት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንጂ ለባለሃብቶች ክፍት አይሰጥም ብለዋል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement