NEWS: የልማት ተነሺዎች ላይ የመብት ጥሰቶች እንደሚፈፀሙ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ

                                                         

በክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ በልማት ምክንያት በሚነሱ ዜጎች ላይ በተለያየ መንገድ የሚፈፀሙ የመብት ጥሰቶች መኖራቸውን በጥናት ማረጋገጡን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ።

ጥናቱ በኦሮሚያና በአማራ ክልል እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ትኩረት ተደርጎ የተዘጋጀ ነው።

ጥናቱ ከተለያዩ የልማት ተነሺ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚነሱ ቅሬታዎችን መነሻ በማድረግ የተሰራ መሆኑንም ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ቅሬታ አቅራቢ የልማት ተነሺዎቹ ለልማት በሚነሱበት ጊዜ በቂ ካሳ እንደማይከፈላቸው፣ ምትክ የመኖሪያ ቤት እና መሰል አገልግሎቱን በአግባቡ እንደማያገኙም ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም ባካሄደው ጥናት በልማት ምክንያት በሚነሱ ዜጎች ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን ጨምሮ በተለያየ መንገድ የመብት ጥሰቶች እንደሚፈፀሙ መለየቱን ገልጿል።

በልማት ተግባራት ከመኖሪያቸው የሚነሱ ዜጎች የካሳ ክፍያ አፈፃፀም፣ የምትክ ቦታ አሰጣጥና የመሰረተ ልማቶች ያልተሟሉባቸው ስፍራዎች በመኖራቸው ምክንያት የመብት ጥሰቶች እየተፈፀሙ መሆኑን ነው ጥናቱ ያመላከተው።

የልማት ተነሺዎቹ የሚሰጣቸው ምትክ ቦታ ማነስ እና በተደጋጋሚ እንዲነሱ መደረጋቸው ሰዎች የተረጋጋ ኑሮን እንዳይኖሩ እያደረገ መሆኑም በጥናቱ ተገልጿል።

ከትናንት ጀምሮም ረቂቅ ጥናቱ ከፌዴራልና ከክልል ለተውጣጡ የስራ ሀላፊዎችና ባለሙያዎቸ ቀርቦ በአዳማ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።

በጥናቱ ላይ ተጨማሪ ግብዓቶች ከተሟሉ በኋላ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበትም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አስታውቋል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement