NEWS: የአማራ፣ የኦሮሚያና አፋር ብሔራዊ ክልል ምክር ቤቶች የጋራ ፎረም ተካሄደ

                                                          

የአማራ፣ የኦሮሚያና የአፋር ብሔራዊ ክልል ምክር ቤቶች የጋራ ፎረም በኮምቦልቻ ከተማ ተካሄደ።

በአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት አስተናጋጅነት በተካሄደው ፎረም በ2009 በጀት ዓመት የተከናወኑ ተግባራት ተገምግመዋል፡፡ 

በፎረሙ በ2010 በጀት ዓመት እቅድ ላይም ውይይት ተደርጓል፡፡ 

የአማራና የአፋር ብሔራዊ ክልል ምክር ቤቶች የሁለቱ ክልሎች አጎራባች ወረዳ ምክር ቤቶች ልማትን በጋራ ለማምጣትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት የህዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ስምምነት ተፈራርመው እየሰሩ መሆኑ ይታወቃል፡፡ 

በ2009 በጀት ዓመት ይህን ስምምነት ወደ ሶስትዮሽ በማሳደግ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ተጎራባች ወረዳዎችም የፎረሙ አካል ሆነው ሥራ መጀመራቸው ነው የተነገረው።

በውይይቱም ስምምነቱ ከሁለትዮሽ ወደ ሶስትዮሽ ማደጉ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እየተጠናከረ እንዲመጣ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች፣ ግጭቶችን ከመፍታትና ወንጀለኞችን ተጠያቂ ከማድረግ አልፎ ወደ ልማት በመግባት ህዝቦች ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲኖራቸው እየተሰሩ መሆኑ ተጠቅሷል።

የእርስ በእርስ ልምድ ልውውጥ እየተደረገ መሆኑ በጥንካሬ የታዩ ጉዳዮች መሆናቸው ተገምግሟል፡፡ 

በሌላ በኩል አልፎ አልፎ በሚፈጠሩ ግጭቶች ወንጀል የሚፈጽሙ ግለሰቦችን ይዞ ለህግ ያለማቅረብ፣ የሚፈጠሩ ችግሮችን በባለቤትነት ከመፍታት ይልቅ ውጫዊ የማድረግና በክላስተር በጋራ ያለመገምገም ችግሮች መኖራቸው ተነስቷል።

የሚካሄዱ ኮንፈረንሶች በሳልና ችግር ፈቺ ያለመሆናቸው በጉድለት የተጠቀሱ ሲሆን፥ ችግሮችን በመፍታት በ2010 በጀት ዓመት በተለይ የቀበሌ መዋቅርን በማጠናከር ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደሚገባ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ 

የቀጣይ አቅጣጫዎች በአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት አፈጉባዔ በአቶ ይርሳው ታምሬ ቀርበዋል።

በአማራና በአፋር መካከል የነበረው የሁለትዮሽ ስምምነት ወደ ሶስትዮሽ የተቀየረበትና የሶስቱ ክልሎች አዋሳኝ ወረዳዎች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማስፋት አርብቶ አደሩና አርሶ አደሩ ተባብረው እንዲለሙ የሚያስችል ሰነድ ቀርቦ በክልሎቹ ምክር ቤት አፈ ጉባዔዎች መፈረሙን ከአማራ ክልል ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement