በሰውነታችን ውስጥ ቀይ የደም ህዋስ መጠን ዝቅተኛ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶችና መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎች

                                                           

ሰዎች በደማቸው ውስጥ የቀይ ደም ህዋሳት መጠን ዝቅተኛ በሚሆንበት ጊዜ ሰውነታቸው በቂ ኦክሲጅን ለማግኘት ከመጠን በላይ ለመስራት ይገደዳል።

ይህ ደግሞ የሰውነት ድርቀትን ያስከትላል።

የቀይ የደም ህዋሳት መጠን ዝቅጠተኛ መሆን ለተለያዩ ችግሮች የሚዳርግ ሲሆን የሚያሳያቸው ምልክቶች አሉ።

ሰዎች ቀይ የደም ህዋሳቸው እንዲጨምር አመጋገብን ከማስተካከል አልፎ ሌሎችንም ተግባራት ሊያከናውኑ ይችላሉ፤ ሆኖም ምልክቶች ካልተወገዱ ሃኪምን ማማከር ይኖርባቸዋል።

ቀይ የደም ህዋሳት በሰዎች ደም ውስጥ በጣም አስፈላጊ ህዋሶች ሲሆኑ፥ በኦክሲጅንን በሰውነት ውስጥ የሚያጓጉዘውን ሄሞግሎቢንን ይዘዋል።

ሄሞግሎቢን ለደም ቀለም መለያየትም ወሳኝ ሚና አለው።

ቀይ የደም ህዋሳት በሰውነት ውስጥ ለ115 ቀናት የሚዘወሩ ሲሆን፥ ከዚያ በኋላ ወደ ጉበት በመግባት ተበታትነው በውስጣቸው ያለው ንጥረነገር ተጠራቅሞ እንደገና ወደ ህዋስነት ይመለሳሉ።

እነዚህ ህዋሳት በዘላቂነት የሚመረቱት ከአጥንት መቅኔ(bone marrow) በመሆኑ፥ ሰውነታችን በቂ ንጥረ ምግብ ካላገኘ የቀይ ደም ህዋሳት መጠን ዝቅተኛ የመሆን እና የመጥፋት ችግር ያጋጥማል።

– ደም ማነስ፣ ከፍተኛ ድካም፣ የሰውነት መዛል፣ የትንፋሽ እጥረት እና የልብ ምት መዛባት የቀይ ደም ህዋስ መጠን በደማችን ውስጥ ዝቅተኛ ሲሆን ከሚታዩ ምልክቶች ዋናዎቹ ናቸው።

በወንዶች ሰውነት ውስጥ መገኘት አለበት ተብሎ የሚገመተው መደበኛ ቀይ የደም ህዋሳት መጠን፥ በማክይሮ ሊትር ከ4 ነጥብ 7 እስከ 6 ነጥብ 1 ሚየሊን ህዋሶች ሲኖሩ ነው።

ለሴቶች ደግሞ ከ4 ነጥብ 2 እስከ 5 ነጥብ 4 ሚሊየን ይደርሳሉ ተብሎ ይገመታል።

የህፃናት ደግሞ ከ4 እስከ 5 ነጥብ 5 ሚሊየን ቀይ የደም ህዋሳት እንደሚደርሱ ተነግሯል።

ይህ የደም ህዋሳቱ መጠን እንደየሰው ሊለያይ ይችላል ነው የተባለው።

በቤተሙከራ የደም ህዋስ ልኬት መሰረትም ከተቀመጠው መጠን ያነሰ ህዋስ ያላቸው ሰዎች ለከፋ የጤና ችግር ተጋላጭ መሆናቸውን ያመላክታል።

ለቀይ የደም ህዋስ መጠን መቀነስ ምክንያት ሊሆኑ ከሚችሉ አጋጣሚዎች መካከል ከፍተኛ የደም መፍሰስ፣ በቂ ንጥረ ምግብ አለመጠቀም፣ የኩላሊት ህመም፣ የአጥንት መቅኔ እጥረት፣ እርግዝና እና የሰውነት ድርቀት ይጠቀሳሉ።

በመሆኑም ቀይ የደም ህዋሳትን ለመጨመር በውስጣቸው አይረን የሚገኝባቸውን እንደ
አሳ፣ ስፒናች፣ ባቄላ፣ ስጋ፣ ምስር፣ የዶሮ ጉበት፣ ቦለቄ እና ሌሎችን የእህልና የስጋ ተዋፅኦዎች መመገብ ይገባል።

በቫይታሚን ቢ-12 የበለፀጉትን ቀይ ስጋ፣ ወተት፣ አይብ፣ አሳ እና መሰል ምግቦችን መጠቀም የቀይ የደም ህዋሳትን መጠን እንዳይቀንስ ያደርጋሉ።

በቫይታሚን ቢ-9፣ ሲ፣ ኤ የበለፀጉ ፍራፍሬዎችን እና የአትክልት ምግቦችን መውሰድም ጠቃሚ መሆኑ ተነግሯል።

የአልኮል መጠንን መቀነስ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስራት ለቀይ የደም ህዋሳት በሰውነታችን ውስጥ በበቂ ሁኔታ መገኘት አስተዋፅጽኦ አላቸው።

በአመጋገብ እና በሌሎች በራስ አቅም በሚሰሩ ተግባራት የማይስተካከል የቀይ የደም ህዋስ መጠን ማነስ ችግር በሚኖርበት ጊዜ የከፋ የጤና ቀውስ ከመፈጠሩ በፊት ሃኪሞችን ማማከር ይገባል ።

ምንጭ:- ጤናችን

Advertisement