NEWS: የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት የአውሮፓ ህብረት ጥምር የጦር ሃይል እንዲኖረው የማሻሻያ ሀሳብ አቀረቡ

                                           

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ስለ አውሮፓ ህብረት የወደፊት ሁኔታ ባቀረቡት የመሻሻያ ሀሳብ ጥምር የጦር ሃይል ሊኖረው እንደሚገባ ተናግረዋል።

ማክሮን በህብረቱ ዙሪያ ጠንካራ ማሻሻያዎችን ያቀረቡ ሲሆን፥ በፀረ ሽብር ትግል እና በፀጥታ ስራዎች ጠንካራ ትብብር መኖር እንዳለበት ነው የጠቆሙት።

ባሳለፍነው ግንቦት ወር ወደ ስልጣን የመጡት ማክሮን የአውሮፓ ቀጠናን ለማጠናከር እና ለብሪታኒያ መውጣት ባሻገር የህብረቱን ውህደት ለማሻሻል እንደሚሰሩ ቃል ገብተው ነበር።

ሆኖም ባለፈው እሁድ በጀርመን ምርጫ የተመዘገበው ውጤት የህብረቱን ህልውና ጥያቄ ውስጥ የሚከት አቋም የሚያንፀባርቁ ፓርቲዎችን በመቀላቀሉ ችግር ሊገጥማቸው እንደሚችል ተጠቁሟል።

ኢማኑኤል ማክሮን ፓሪስ በሚገኘው ሶርቦኔ ዩኒቨርሲቲ ባደረጉት ንግግር የአውሮፓ ህብረት በራሱ የሚመራ ጥምር ወታደራዊ ሃይል ሊኖረው እንደሚገባ ነው የገለጹት።

ለዚህም ሀገራት የጋራ የመከላከያ በጀት እንዲመድቡ እና ፖሊሲ በመቅረፅ የአውሮፓ ወታደራዊ የስልጠና ትምህርት ቤት እንዲቋቋምም ጥሪ አቅርበዋል።

ፕሬዚዳንቱ በህብረቱ ዙሪያ ባቀረቡት ማሻሻያ ሀሳብ የአርንጓዴ ቴክኖሎጂ እድገትን፣ የካርቦን ልቀት ቅነሳን፣ የጋራ የግብርና ፖሊሲ መቅረጽን፣ እና ሌሎችንም ጉዳዮች አካተዋል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

 

Advertisement